መጽሐፈ፡ኢዮብ።

(ክለሳ.1.20020507)

_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡1።______________
ምዕራፍ፡1።
1፤ዖፅ፡በሚባል፡አገር፡ስሙ፡ኢዮብ፡የተባለ፡አንድ፡ሰው፡ነበረ፤ያም፡ሰው፡ፍጹምና፡ቅን፥እግዚአብሔርንም፡የ ሚፈራ፥ከክፋትም፡የራቀ፡ነበረ።
2፤ሰባትም፡ወንዶች፡ሦስትም፡ሴቶች፡ልጆች፡ተወልደውለት፡ነበር።
3፤ሀብቱም፡ሰባት፡ሺሕ፡በጎች፥ሦስት፡ሺሕም፡ግመሎች፥ዐምስት፡መቶም፡ጥማድ፡በሬ፥ዐምስት፡መቶም፡እንስት፡አ ህያዎች፡ነበረ፥እጅግ፡ብዙም፡ባሪያዎች፡ነበሩት፤ያም፡ሰው፡በምሥራቅ፡ካሉ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይልቅ፡ታላቅ፡ነበረ ።
4፤ወንዶች፡ልጆቹም፡ኼደው፡በየተራ፡በያንዳንዳቸው፡ቤት፡ግብዣ፡ያደርጉ፡ነበር፤ሦስቱ፡እኅቶቻቸውም፡ከነርሱ ፡ጋራ፡ይበሉና፡ይጠጡ፡ዘንድ፡እነርሱ፡ልከው፡ይጠሯቸው፡ነበር።
5፤የግብዣውም፡ቀኖች፡ባለፉ፡ጊዜ፡ኢዮብ፦ምናልባት፡ልጆቼ፡በድለው፥እግዚአብሔርንም፡በልባቸው፡ሰድበው፡ይኾ ናል፡ብሎ፡ይልክና፡ይቀድሳቸው፡ነበር፤ኢዮብም፡ማልዶ፡ተነሣ፥እንደ፡ቍጥራቸውም፡ዅሉ፡የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ አቀረበ።እንዲሁ፡ኢዮብ፡ዅልጊዜ፡ያደርግ፡ነበር።
6፤ከዕለታት፡አንድ፡ቀን፡እንዲህ፡ኾነ፤የአምላክ፡ልጆች፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለመቆም፡መጡ፥ሰይጣንም፡ደግሞ ፡በመካከላቸው፡መጣ።
7፤እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦ከወዴት፡መጣኽ፧አለው።ሰይጣንም፦ምድርን፡ዅሉ፡ዞርዃት፥በርሷም፡ተመላለስኹ፡ብ ሎ፡ለእግዚአብሔር፡መለሰ።
8፤እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦በእውኑ፡ባሪያዬን፡ኢዮብን፡ተመለከትኸውን፧በምድር፡ላይ፡እንደ፡ርሱ፡ፍጹምና፡ ቅን፥እግዚአብሔርንም፡የሚፈራ፥ከክፋትም፡የራቀ፡ሰው፡የለም፡አለው።
9፤ሰይጣንም፡ለእግዚአብሔር፡እንዲህ፡ብሎ፡መለሰለት፦በእውኑ፡ኢዮብ፡እግዚአብሔርን፡የሚፈራ፡በከንቱ፡ነውን ፧
10፤ርሱንና፡ቤቱን፡በዙሪያውም፡ያሉትን፡ዅሉ፡አላጠርኽለትምን፧የእጁን፡ሥራ፡ባርከኽለታል፥ከብቱም፡በምድር ፡ላይ፡በዝቷል።
11፤ነገር፡ግን፥እጅኽን፡ዘርግተኽ፡ያለውን፡ዅሉ፡ዳብስ፤በእውነት፡በፊትኽ፡ይሰድብኻል።
12፤እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦እንሆ፥ለርሱ፡ያለው፡ዅሉ፡በእጅኽ፡ነው፥ነገር፡ግን፥በርሱ፡ላይ፡እጅኽን፡አት ዘርጋ፡አለው።ሰይጣንም፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡ወጣ።
13፤አንድ፡ቀንም፡እንዲህ፡ኾነ፤የኢዮብ፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆች፡በታላቅ፡ወንድማቸው፡ቤት፡ይበሉና፡የወይን ፡ጠጅ፡ይጠጡ፡ነበር።
14፤መልክተኛም፡ወደ፡ኢዮብ፡መጥቶ፦በሬዎች፡ዕርሻ፡ያርሱ፥በአጠገባቸውም፡አህያዎች፡ይሰማሩ፡ነበር፤
15፤የሳባም፡ሰዎች፡አደጋ፡ጣሉ፥ወሰዷቸውም፥ብላቴናዎቹንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ገደሉ፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።
16፤ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ሌላ፡መጥቶ፦የእግዚአብሔር፡እሳት፡ከሰማይ፡ወደቀች፥በጎቹንም፡አቃጠለች፥ጠባቂዎች ንም፡በላች፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።
17፤ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ሌላ፡መጥቶ፦ከለዳውያን፡በሦስት፡ረድፍ፡ተከፍለው፡በግመሎች፡ላይ፡አደጋ፡ጣሉ፥ወሰ ዷቸውም፥ብላቴናዎቹንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ገደሉ፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።
18፤ርሱም፡ገና፡ሲናገር፡ሌላ፡መጥቶ፦ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆችኽ፡በታላቅ፡ወንድማቸው፡ቤት፡ይበሉና፡የወይን፡ ጠጅ፡ይጠጡ፡ነበር፤
19፤እንሆም፥ዐውሎ፡ነፋስ፡ከምድረ፡በዳ፡መጥቶ፡የቤቱን፡አራቱን፡ማእዘን፡መታው፥በብላቴናዎቹም፡ላይ፡ወደቀ ፥ሞቱም፤እኔም፡እነግርኽ፡ዘንድ፡ብቻዬን፡አመለጥኹ፡አለው።
20፤ኢዮብም፡ተነሣ፡መጐናጸፊያውንም፡ቀደደ፥ራሱንም፡ተላጨ፥በምድርም፡ላይ፡ተደፍቶ፡ሰገደ፤
21፤እንዲህም፡አለ፦ዕራቍቴን፡ከእናቴ፡ማሕፀን፡ወጥቻለኹ፥ዕራቍቴንም፡ወደዚያ፡እመለሳለኹ፤እግዚአብሔር፡ሰ ጠ፥እግዚአብሔርም፡ነሣ፤የእግዚአብሔር፡ስም፡የተባረከ፡ይኹን።
22፤በዚህ፡ዅሉ፡ኢዮብ፡አልበደለም፥ለእግዚአብሔርም፡ስንፍናን፡አልሰጠም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡2።______________
ምዕራፍ፡2።
1፤ከዕለታት፡አንድ፡ቀን፡እንዲህ፡ኾነ፤የአምላክ፡ልጆች፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለመቆም፡መጡ፥ሰይጣን፡ደግሞ፡ በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለመቆም፡በመካከላቸው፡መጣ።
2፤እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦ከወዴት፡መጣኽ፧አለው።ሰይጣንም፦በምድር፡ላይ፡ዞርኹ፥በርሷም፡ተመላለስኹ፡ብሎ ፡ለእግዚአብሔር፡መለሰ።
3፤እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦በእውኑ፡ባሪያዬን፡ኢዮብን፡ተመለከትኸውን፧በምድር፡ላይ፡እንደ፡ርሱ፡ፍጹምና፡ ቅን፥እግዚአብሔርንም፡የሚፈራ፥ከክፋትም፡የራቀ፡ሰው፡የለም፤በከንቱም፡አጠፋው፡ዘንድ፡አንተ፡በርሱ፡ላይ፡ ምንም፡ብታንቀሳቅሰኝ፥እስከ፡አኹን፡ፍጹምነቱን፡ይዟል።
4፤ሰይጣንም፡መልሶ፡እግዚአብሔርን፦ቍርበት፡ስለ፡ቍርበት፡ነው፤ሰው፡ያለውን፡ዅሉ፡ስለ፡ሕይወቱ፡ይሰጣል።
5፤ነገር፡ግን፥አኹን፡እጅኽን፡ዘርግተኽ፡ዐጥንቱንና፡ሥጋውን፡ዳብስ፤በእውነት፡በፊትኽ፡ይሰድብኻል፡አለው።
6፤እግዚአብሔርም፡ሰይጣንን፦ሕይወቱን፡ተወው፡እንጂ፥እንሆ፥ርሱ፡በእጅኽ፡ነው፡አለው።
7፤ሰይጣንም፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡ወጣ፥ኢዮብንም፡ከእግሩ፡ጫማ፡ዠምሮ፡እስከ፡ዐናቱ፡ድረስ፡በክፉ፡ቍስል፡መ ታው።
8፤ሥጋውንም፡ይፍቅበት፡ዘንድ፡ገል፡ወሰደ፥በዐመድም፡ላይ፡ተቀመጠ።
9፤ሚስቱም፦እስከ፡አኹን፡ፍጹምነትኽን፡ይዘኻልን፧እግዚአብሔርን፡ስደብና፡ሙት፡አለችው።
(የሚቀጥለው፡ከግሪክ፡የተጨመረ፡ነው)፡
ዳግመኛ፡እግዚአብሔርን፡ጥቂት፡ወራት፡ደጅ፡እጠናዋለኹ፤ዳግመኛም፡መከራውን፡እታገሠዋለኹ፥የቀድሞ፡ኑሮዬን ም፡ተስፋ፡አደርገዋለኹ፡ትላለኽን፧አለችው።እንደዚህሳ፡እንዳትል፡ከዚህ፡ዓለም፥እንሆ፥ስም፡አጠራርኽ፡ጠፋ ፤ሴቶች፡ልጆቼና፡ወንዶች፡ልጆቼም፡ሞቱ፡እኔስ፡ዘጠኝ፡ወር፡ሳረግዝ፡ሳምጥ፡ስወልድ፡ሳይረቡኝ፡ሳይጠቅሙኝ፡ በከንቱ፡ደከምኹ፡አለች።አንተም፡በመግል፡ተውጠኽ፡በትል፡ተከበ፟ኽ፡ትኖራለኽ፤ሌሊቱን፡ዅሉ፡ስትዛብር፡ታድ ራለኽ።እኔ፡ግን፡እየዞርኹ፡እቀላውጣለኹ።ከአንዱ፡አገር፡ወደ፡አንዱ፡አገር፡ከአንዱ፡ቤት፡ወደ፡አንዱ፡ቤት ፡እኼዳለኹ፤ከድካሜ፡በእኔ፡ላይ፡ካለ፡ከችግሬም፡ዐርፍ፡ዘንድ፡ከጧት፡ዠምሮ፡ፀሓይ፡እስኪገባ፡ድረስ፡እጠብ ቃለኹ፤አኹን፡ግን፡እግዚአብሔርን፡የማይገ፟ባ፟፡ቃል፡ተናግረኸው፡ሙት፡አለች።
10፤ርሱ፡ግን፡አንቺ፡ከሰነፎች፡ሴቶች፡እንደ፡አንዲቱ፡ተናገርሽ፤ከእግዚአብሔር፡እጅ፡መልካሙን፡ተቀበልን፥ ክፉ፡ነገርንስ፡አንቀበልምን፧አላት።በዚህ፡ዅሉ፡ኢዮብ፡በከንፈሩ፡አልበደለም።
11፤ሦስቱም፡የኢዮብ፡ወዳጆች፡ይህን፡የደረሰበትን፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡ሰምተው፡ከየአገራቸው፡መጡ፤እነርሱም፡ ቴማናዊው፡ኤልፋዝ፥ሹሐዊው፡በልዳዶስ፥ነዕማታዊው፡ሶፋር፡ነበሩ።እነርሱም፡ሊያዝኑለትና፡ሊያጽናኑት፡በአን ድነት፡ወደ፡ርሱ፡ለመምጣት፡ተስማሙ።
12፤ከሩቅም፡ኾነው፡ዐይናቸውን፡ባነሡ፡ጊዜ፡አላወቁትም፤ድምፃቸውንም፡አሰምተው፡አለቀሱ፤እያንዳንዳቸውም፡ መጐናጸፊያቸውን፡ቀደዱ፥ወደ፡ላይም፡ወደ፡ራሳቸው፡ላይ፡ትቢያ፡ነሰነሱ።
13፤ሰባት፡ቀንና፡ሰባት፡ሌሊትም፡ከርሱ፡ጋራ፡በምድር፡ላይ፡ተቀመጡ፤ሕመሙም፡እጅግ፡እንደ፡በዛ፡አይተዋልና ፥ከነርሱ፡አንድ፡ቃል፡የሚናገረው፡አልነበረም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡3።______________
ምዕራፍ፡3።
1፤ከዚያም፡በዃላ፡ኢዮብ፡አፉን፡ከፍቶ፡የተወለደበትን፡ቀን፡ረገመ።
2፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህ፡አለ፦
3፤ያ፡የተወለድኹበት፡ቀን፡ይጥፋ፥
ያም፦ወንድ፡ልጅ፡ተፀነሰ፡የተባለበት፡ሌሊት።
4፤ያ፡ቀን፡ጨለማ፡ይኹን፤
እግዚአብሔር፡ከላይ፡አይመልከተው፥
ብርሃንም፡አይብራበት።
5፤ጨለማና፡የሞት፡ጥላ፡የራሳቸው፡ገንዘብ፡ያድርጉት፤
ዳመናም፡ይረፍበት፤
የቀን፡ጨለማ፡ዅሉ፡ያስፈራው።
6፤ያን፡ሌሊት፡ጨለማ፡ይያዘው፤
በዓመቱ፡ቀኖች፡መካከል፡ደስ፡አይበለው፤
በወሮች፡ውስጥ፡ገብቶ፡አይቈጠር።
7፤እንሆ፥ያ፡ሌሊት፡መካን፡ይኹን፤
እልልታ፡አይግባበት።
8፤ሌዋታንን፡ለማንቀሳቀስ፡የተዘጋጁ፡
ቀኑን፡የሚረግሙ፡ይርገሙት።
9፤አጥቢያ፡ኮከቦች፡ይጨልሙ፤
ብርሃንን፡ቢጠባበቅ፡አያግኘው፥
የንጋትንም፡ቅንድብ፡አይይ፤
10፤የእናቴን፡ማሕፀን፡ደጅ፡አልዘጋምና፥
መከራንም፡ከዐይኔ፡አልሰወረምና።
11፤በማሕፀን፡ሳለኹ፡ስለ፡ምን፡አልሞትኹም፧
ከሆድስ፡በወጣኹ፡ጊዜ፡ፈጥኜ፡ስለ፡ምን፡አልጠፋኹም፧
12፤ጕልበቶች፡ስለ፡ምን፡ተቀበሉኝ፧
ጡትስ፡ስለ፡ምን፡ጠባኹ፧
13፤አኹን፡ተኝቼ፡ዝም፡ባልኹ፡ነበር፤
አንቀላፍቼ፡ባረፍኹ፡ነበር፤
14፤የፈረሰውን፡ለራሳቸው፡ከሚሠሩት፡
ከምድር፡ነገሥታትና፡መካሮች፡ጋራ፥
15፤ወይም፡ቤታቸውን፡ብር፡ከሞሉ፡
ወርቅም፡ካላቸው፡መኳንንት፡ጋራ፥
16፤ወይም፡እንደ፡ተቀበረ፡ጭንጋፍ፥
ብርሃንም፡እንዳላዩ፡ሕፃናት፡በኾንኹ፡ነበር።
17፤ክፉዎች፡በዚያ፡መናደዳቸውን፡ይተዋሉ፤
በዚያም፡ደካማዎች፡ያርፋሉ።
18፤በዚያ፡ግዞተኛዎች፡በአንድነት፡ተዘልለው፡ተቀምጠዋል፤
የአስጨናቂውን፡ድምፅ፡አይሰሙም።
19፤ታናሽና፡ታላቅ፡በዚያ፡አሉ፤
ባሪያም፡ከጌታው፡ነጻ፡ወጥቷል።
20፤በመከራ፡ላሉት፡ብርሃን፥
ነፍሳቸው፡መራራ፡ለኾነችባቸው፥
21፤የተሰወረ፡ሀብትን፡ከሚቈፍሩ፡ይልቅ፡
ሞትን፡ለሚጠብቁ፡ለማያገኙትም፥
22፤መቃብርን፡ባገኙ፡ጊዜ፡
በእልልታ፡ደስ፡ለሚላቸው፥ሐሤትንም፡ለሚያደርጉ፡
ሕይወት፡ስለ፡ምን፡ተሰጠ፧
23፤መንገዱ፡ለተሰወረበት፡ሰው፥
እግዚአብሔርም፡በዐጥር፡ላጠረው፡
ብርሃን፡ስለ፡ምን፡ተሰጠ፧
24፤ከእንጀራዬ፡በፊት፡ልቅሶዬ፡መጥቷልና፥
ጩኸቴም፡እንደ፡ውሃ፡ፈስሷል።
25፤የፈራኹት፡ነገር፡መጥቶብኛልና፥
የደነገጥኹበትም፡ደርሶብኛል።
26፤ተዘልዬ፡አልተቀመጥኹም፥አልተማመንኹም፥አላረፍኹም፤
ነገር፡ግን፡መከራ፡መጣብኝ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡4።______________
ምዕራፍ፡4።
1፤ቴማናዊውም፡ኤልፋዝ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤አንድ፡ሰው፡ከአንተ፡ጋራ፡ይናገር፡ዘንድ፡ቢሞክር፡ትቀየማለኽን፧
ቃልንስ፡ከመናገር፡ሊቀር፡የሚችል፡ማን፡ነው፧
3፤እንሆ፥አንተ፡ብዙዎችን፡ታስተምር፡ነበር፥
የደከሙትንም፡እጆች፡ታበረታ፡ነበር፥
4፤ቃልኽ፡የሚሰናከለውን፡ያስነሣ፡ነበር፥
አንተም፡የሚብረከረከውን፡ጕልበት፡ታጸና፡ነበር።
5፤አኹን፡ግን፡ባንተ፡ላይ፡መጥቷል፥አንተም፡ደከምኽ፤
ደርሶብኻል፥አንተም፡ተቸገርኽ።
6፤አምላክኽን፡መፍራትኽ፡መጽናናትኽ፥
የቅንነትኽም፡መንገድ፡ተስፋኽ፡አይደለምን፧
7፤እባክኽ፡ዐስብ፥ንጹሕ፡ኾኖ፡የጠፋ፡ማን፡ነው፧
ከልበ፡ቅንስ፡የተደመሰሰ፡ማን፡ነው፧
8፤እኔ፡እንዳየኹ፥ኀጢአትን፡የሚያርሱ፥
መከራንም፡የሚዘሩ፡ይህንኑ፡ያጭዳሉ።
9፤በእግዚአብሔር፡እስትንፋስ፡ይጠፋሉ፥
በቍጣውም፡መንፈስ፡ያልቃሉ።
10፤የአንበሳ፡ጩኸት፥የጯኺ፡አንበሳ፡ድምፅ፥
የአንበሳ፡ደቦል፡ጥርስ፡ተሰባበረ።
11፤አሮጌ፡አንበሳ፡አደን፡በማጣት፡ይሞታል፥
የአንበሳዪቱም፡ግልገሎች፡ይበተናሉ።
12፤ለኔም፡በምስጢር፡ቃል፡መጣልኝ፥
ዦሮዬም፡ሹክሹክታውን፡ሰማች።
13፤በሌሊት፡ሕልም፡ዐሳብ፡ሲነሣ፥
የከበደም፡እንቅልፍ፡በሰው፡ላይ፡ሲወድቅ፥
14፤ዐጥንቴን፡ዅሉ፡ያናወጡ፡
ድንጋጤና፡መንቀጥቀጥ፡ወደቁብኝ።
15፤መንፈስም፡በፊቴ፡ዐለፈ፤
የሥጋዬ፡ጠጕር፡ቆመ።
16፤ርሱም፡ቆመ፥መልኩን፡ግን፡ለመለየት፡አልቻልኹም፥
ምሳሌም፡በዐይኔ፡ፊት፡ነበረ፤
የዝምታ፡ድምፅ፡ሰማኹ።
17፤በእውኑ፡ሰው፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ጻድቅ፡ሊኾን፥
ወይስ፡ሰው፡በፈጣሪው፡ፊት፡ሊነጻ፡ይችላልን፧
18፤እንሆ፥በባሪያዎቹ፡አይታመንም፤
መላእክቱንም፡ስንፍና፡ይከሳ፟ቸዋል፤
19፤ይልቁንስ፡በጭቃ፡ቤት፡የሚኖሩ፥
መሠረታቸው፡በትቢያ፡ውስጥ፡የኾነ፥
ከብል፡በፊት፡የሚጨፈለቁ፡እንዴት፡ይኾኑ፧
20፤በጧትና፡በማታ፡መካከል፡ይሰባበራሉ፤
ማንም፡ሳያስብ፡ለዘለዓለም፡ይጠፋሉ።
21፤ገመዳቸው፡የተነቀለ፡አይደለምን፧
አለጥበብም፡ይሞታሉ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡5።______________
ምዕራፍ፡5።
1፤አኹንም፡ጥራ፤የሚመልስልኽ፡አለን፧
ከቅዱሳንስ፡ወደ፡ማናቸው፡ትዞራለኽ፧
2፤ሰነፉን፡ሰው፡ቍጣ፡ይገድለዋል፥
ሰነፉንም፡ቅንአት፡ያጠፋዋል።
3፤ሰነፍ፡ሰው፡ሥር፡ሰዶ፟፡አየኹት፥
ድንገትም፡መኖሪያውን፡ረገምኹ።
4፤ልጆቹም፡ከደኅንነት፡ርቀዋል፥
በበርም፡ውስጥ፡ተረግጠዋል፥
የሚታደጋቸውም፡የለም።
5፤የሰበሰበውንም፡ራብተኛ፡ይበላዋል፥
ከሾኽም፡ውስጥ፡እንኳ፡ያወጣዋል፤
የተጠማ፡ሀብታቸውን፡ዋጠ።
6፤ችግር፡ከትቢያ፡አይመጣም፥
መከራም፡ከመሬት፡አይበቅልም፤
7፤የአሞራ፡ግልገሎች፡ግን፡ወደ፡ላይ፡እየበረሩ፡ከፍ፡እንዲሉ፥
ሰው፡እንዲሁ፡ለመከራ፡ተወልዷል።
8፤እኔ፡ግን፡እግዚአብሔርን፡እለምን፡ነበር፥
ነገሬንም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡አቀርብ፡ነበር።
9፤የማይመረመረውን፡ታላቅ፡ነገርና፡
የማይቈጠረውን፡ተኣምራት፡ያደርጋል።
10፤በምድር፡ላይ፡ዝናብን፡ይሰጣል፥
በዕርሻም፡ላይ፡ውሃ፡ይልካል።
11፤የተዋረዱትን፡ወደ፡ላይ፡ያወጣል፥
ሐዘንተኛዎችንም፡ለደኅንነት፡ከፍ፡ከፍ፡ያደርጋቸዋል።
12፤እጃቸውም፡ምክራቸውን፡እንዳይፈጽም፡
የተንኰለኛዎችን፡ዐሳብ፡ከንቱ፡ያደርገዋል።
13፤ጠቢባንን፡በተንኰላቸው፡ይይዛቸዋል፤
የጠማማዎችንም፡ምክር፡ይዘረዝራል።
14፤በቀን፡ጨለማን፡ያገኛሉ፥
በቀትርም፡ጊዜ፡በሌሊት፡እንዳሉ፡ይርመሰመሳሉ።
15፤ድኻውንም፡ከአፋቸው፡ሰይፍ፡
ከኀያሉም፡እጅ፡ያድነዋል።
16፤ለምስኪኑም፡ተስፋ፡አለው፤
ክፋት፡ግን፡አፏን፡ትዘጋለች።
17፤እንሆ፥እግዚአብሔር፡የሚገሥጸው፡ሰው፡ምስጉን፡ነው፤
ስለዚህ፡ዅሉን፡የሚችለውን፡የአምላክን፡ተግሣጽ፡አትናቅ።
18፤ርሱ፡ይሰብራል፥ይጠግንማል፤
ያቈስላል፥እጆቹም፡ይፈውሳሉ።
19፤በስድስት፡ክፉ፡ነገር፡ውስጥ፡ያድንኻል፥
በሰባትም፡ውስጥ፡ክፋት፡አትነካኽም።
20፤በራብ፡ጊዜ፡ከሞት፥
በሰልፍም፡ከሰይፍ፡እጅ፡ያድንኻል።
21፤ከምላስ፡ጅራፍ፡ትሰወራለኽ፤
ጥፋትም፡ሲመጣ፡አትፈራም።
22፤በጥፋትና፡በራብ፡ላይ፡ትሥቃለኽ፤
ከምድረ፡በዳ፡አራዊትም፡አትፈራም፤
23፤ቃል፡ኪዳንኽ፡ከምድረ፡በዳ፡ድንጋይ፡ጋራ፡ይኾናልና፤
የምድረ፡በዳም፡አራዊት፡ከአንተ፡ጋራ፡ይስማማሉና።
24፤ድንኳንኽም፡በሰላም፡እንዲኾን፡ታውቃለኽ፤
በረትኽን፡ትጐበኛለኽ፡አንዳችም፡አይጐድልብኽም።
25፤ዘርኽም፡ታላቅ፡እንዲኾን፥
ትውልድኽም፡እንደምድር፡ሣር፡እንዲኾን፡ታውቃለኽ።
26፤በወራቱ፡የእኽሉ፡ነዶ፡ወደ፡ዐውድማ፡እንዲገባ፥
በረዥም፡ዕድሜ፡ወደ፡መቃብር፡ትገባለኽ።
27፤እንሆ፥ይህችን፡መረመርን፥የሰማነውም፡ይህ፡ነው፤
አንተ፡ግን፡አንዳች፡ሠርተኽ፡እንደ፡ኾነ፡ለራስኽ፡ዕወቀው።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡6።______________
ምዕራፍ፡6።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ።
2፤ትካዜዬ፡ምነው፡በተመዘነ፡ኖሮ!
መከራዬም፡ዅሉ፡ምነው፡በሚዛን፡ላይ፡በተደረገ፡ኖሮ!
3፤ከባሕር፡አሸዋ፡ይልቅ፡ይከብድ፡ነበርና፤
ስለዚህ፡ቃሌ፡ደፋር፡ኾኗል።
4፤ዅሉን፡የሚችል፡የአምላክ፡ፍላጻ፡በሥጋዬ፡ውስጥ፡ነው፥
መርዙንም፡ነፍሴ፡ትጠጣለች፤
የእግዚአብሔር፡ድንጋጤ፡በላዬ፡ተሰልፏል።
5፤በእውኑ፡የሜዳ፡አህያ፡ሣር፡ሳለው፡ይጮኻልን፧
ወይስ፡በሬ፡ገለባ፡ሳለው፡ይጮኻልን፧
6፤የማይጣፍጥስ፡ነገር፡ያለጨው፡ይበላልን፧
ወይስ፡የዕንቍላል፡ውሃ፡ይጥማልን፧
7፤ሰውነቴ፡ትነካው፡ዘንድ፡እንቢ፡አለችው፤
እንደሚያስጸይፍ፡መብል፡ኾነብኝ።
8፤ልመናዬ፡ምነው፡በደረሰልኝ!
እግዚአብሔርም፡ምኞቴን፡ምነው፡በሰጠኝ!
9፤እግዚአብሔርም፡ያደቀኝ፡ዘንድ፡
እጁንም፡ለቆ፟፡ያጠፋኝ፡ዘንድ፡ወዶ፟፡ቢኾን፡ኖሮ!
10፤መጽናናት፡በኾነልኝ፡ነበር፤
በማይራራ፡ሕመም፡ሐሤት፡ባደረግኹ፡ነበር፥
የቅዱሱን፡ቃል፡አልካድኹምና።
11፤እጠብቅ፡ዘንድ፡ጕልበቴ፡ምንድር፡ነው፧
እታገሥም፡ዘንድ፡ፍጻሜዬ፡ምንድር፡ነው፧
12፤ጕልበቴ፡የድንጋይ፡ጕልበት፡ነውን፧
ሥጋዬስ፡እንደ፡ናስ፡ነውን፧
13፤በእውኑ፡ረድኤት፡በእኔ፡እንደሌለ፡
ጥበብም፡ዅሉ፡ከእኔ፡ዘንድ፡እንደ፡ተባረረ፡አይደለምን፧
14፤ዅሉን፡የሚችለውን፡የአምላክን፡መፍራት፡
ለሚተው፥ለመዛል፡ለቀረበው፡ስንኳ፡
ወዳጁ፡ቸርነትን፡ሊያሳይ፡ይገ፟ባ፟ል።
15፤ወንድሞቼ፡እንደ፡ፈፋ፥
እንደሚያልፍ፡ፈፋ፡ሐሰተኛዎች፡ኾኑብኝ።
16፤ከበረዶ፡የተነሣ፡ደፈረሱ፥
ዐመዳይም፡ተሰወረባቸው፤
17፤ፀሓይ፡በተኰሰች፡ጊዜ፡ይደርቃሉ፤
በሙቀትም፡ጊዜ፡ከስፍራቸው፡ይጠፋሉ።
18፤በየዳርቻቸውም፡የሚኼዱ፡ነጋዴዎች፡ፈቀቅ፡ይላሉ፤
ወደ፡በረሓ፡ወጥተው፡ይጠፋሉ።
19፤የቴማን፡ነጋዴዎች፡ተመለከቱ፥
የሳባ፡መንገደኛዎችም፡ተጠባበቋቸው።
20፤ተስፋ፡አድርገዋቸው፡ነበርና፥ዐፈሩ፤
ወደዚያ፡ደረሱ፥ዕፍረትም፡ያዛቸው።
21፤አኹንም፡እናንተ፡እንደዚሁ፡ኾናችዃል፤
መከራዬን፡አይታችኹ፡ፈራችኹ።
22፤በእውኑ፦አንዳች፡ነገር፡አምጡልኝ፤
ወይስ፦ከብልጥግናችኹ፡ስጦታ፡አቅርቡልኝ፤
23፤ወይስ፦ከጠላቴ፡እጅ፡አስጥሉኝ፤
ወይስ፦ካስጨናቂው፡እጅ፡አድኑኝ፡አልዃችኹን፧
24፤አስተምሩኝ፥እኔም፡ዝም፡እላለኹ፤
የተሳሳትኹትንም፡ንገሩኝ።
25፤የቅንነት፡ቃል፡እንዴት፡ኀይለኛ፡ነው!
የእናንተ፡ሙግት፡ግን፡ምን፡ይገሥጻል፧
26፤ተስፋ፡የሌለው፡ሰው፡ንግግር፡እንደ፡ነፋስ፡ነውና፥
ቃሌን፡ትገሥጹ፡ዘንድ፡ታስባላችኹን፧
27፤በድኻ፡አደጉ፡ላይ፡ዕጣ፡ትጣጣላላችኹ፤
ለወዳጆቻችኹም፡ጕድጓድ፡ትቈፍራላችኹ።
28፤አኹንም፥እባካችኹ፥ወደ፡እኔ፡ተመልከቱ፤
በፊታችኹም፡ሐሰት፡አልናገርም።
29፤እባካችኹ፥ተመለሱ፤በደል፡አይኹን፤
ጽድቄ፡በዚህ፡ነገር፡ነውና፥አንድ፡ጊዜ፡ተመለሱ።
30፤በእውኑ፡በአንደበቴ፡በደል፡ይገኛልን፧
አፌስ፡ተንኰልን፡ይለይ፡ዘንድ፡አይችልምን፧
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡7።______________
ምዕራፍ፡7።
1፤በምድር፡ላይ፡የሰው፡ሕይወት፡ብርቱ፡ሰልፍ፡አይደለምን፧
ወራቱም፡እንደ፡ምንደኛ፡ወራት፡አይደለምን፧
2፤አገልጋይ፡ጥላ፡እንደሚመኝ፥
ምንደኛም፡ደመ፡ወዙን፡እንደሚጠብቅ፥
3፤እንዲሁ፡ዕጣዬ፡የከንቱ፡ወራት፡ኾነብኝ፥
የድካምም፡ሌሊት፡ተወሰነችልኝ።
4፤በተኛኹ፡ጊዜ፦መቼ፡እነሣለኹ፧እላለኹ።
ሌሊቱ፡ግን፡ይረዝማል፥
እስኪነጋ፡ድረስም፡እገለባበጣለኹ።
5፤ሥጋዬ፡ትልና፡ጓል፡ለብሷል፤
ቍርበቴ፡ያፈከፍካል፡እንደ፡ገናም፡ይመግላል።
6፤ዘመኔ፡ከሸማኔ፡መወርወሪያ፡ይልቅ፡ይቸኵላል፥
ያለ፡ተስፋም፡ያልቃል።
7፤ሕይወቴ፡እስትንፋስ፡እንደ፡ኾነ፡ዐስብ፤
ዐይኔ፡መልካም፡ነገርን፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አያይም።
8፤የሚያየኝ፡ሰው፡ዐይን፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አያየኝም፤
ዐይንኽ፡በእኔ፡ላይ፡ይኾናል፥እኔም፡አልገኝም።
9፤ደመና፡ተበትኖ፡እንደሚጠፋ፥
እንዲሁ፡ወደ፡ሲኦል፡የሚወርድ፡ዳግመኛ፡አይወጣም።
10፤ወደ፡ቤቱ፡ዳግመኛ፡አይመለስም፥
ስፍራውም፡ዳግመኛ፡አያውቀውም።
11፤ስለዚህም፡አፌን፡አልከለክልም፤
በመንፈሴ፡ጭንቀትን፡እናገራለኹ፤
በነፍሴ፡ምሬት፡በሐዘን፡አንጐራጕራለኹ።
12፤ጠባቂ፡ታስነሣብኝ፡ዘንድ፥
እኔ፡ባሕር፡ወይስ፡ዐንበሪ፡ነኝን፧
13፤እኔም፦ዐልጋዬ፡ያጽናናኛል፥
መኝታዬም፡የሐዘን፡እንጕርጕሮዬን፡ያቀልልኛል፡ባልኹ፡ጊዜ፥
14፤አንተ፡በሕልም፡ታስፈራራኛለኽ፥
በራእይም፡ታስደነግጠኛለኽ፤
15፤ነፍሴም፡ከዐጥንቴ፡ይልቅ፡
መታነቅንና፡ሞትን፡መረጠች።
16፤ሕይወቴን፡ናቅዃት፤ለዘለዓለም፡ልኖር፡አልወድ፟ም።
የሕይወቴ፡ዘመን፡እስትንፋስ፡ነውና፥ተወኝ።
17፤ሰው፡ምንድር፡ነው፡ታከብረው፡ዘንድ፥
ልብኽንስ፡ትጥልበት፡ዘንድ፥
18፤ማለዳ፡ማለዳስ፡ትጐበኘው፡ዘንድ፥
ዅልጊዜስ፡ትፈታተነው፡ዘንድ፧
19፤የማትተወኝ፡እስከ፡መቼ፡ነው፧
ምራቄንስ፡እስክውጥ፡ድረስ፡የማትለቀ፟ኝ፡እስከ፡መቼ፡ነው፧
20፤ሰውን፡የምትጠብቅ፡ሆይ፥በድዬስ፡እንደ፡ኾነ፡ምን፡ላድርግልኽ፧
ስለ፡ምን፡እኔን፡ለአንተ፡ዐላማ፡አደረግኸኝ፧
ስለ፡ምን፡እኔ፡ሸክም፡ኾንኩብኽ፧
21፤ስለ፡ምን፡መተላለፌን፡ይቅር፡አትልም፧
ኀጢአቴንስ፡ስለ፡ምን፡አታስወግድልኝም፧
አኹን፡በምድር፡ውስጥ፡እተኛለኹ፤
ማለዳ፡ትፈልገኛለኽ፥አታገኘኝም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡8።______________
ምዕራፍ፡8።
1፤ሹሐዊውም፡በልዳዶስ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤እስከ፡መቼ፡ይህን፡ትናገራለኽ፧
የአፍኽስ፡ቃል፡እስከ፡መቼ፡እንደ፡ዐውሎ፡ነፋስ፡ይኾናል፧
3፤በእውኑ፡እግዚአብሔር፡ፍርድን፡ያጣምማልን፧
ዅሉንም፡የሚችል፡አምላክ፡ጽድቅን፡ያጣምማልን፧
4፤ልጆችኽ፡በድለውት፡እንደ፡ኾነ፥
ርሱ፡በበደላቸው፡እጅ፡ጥሏቸዋል።
5፤እግዚአብሔርን፡ብትገሠግሥ፥
ዅሉንም፡የሚችለውን፡አምላክ፡ብትለምን፥
6፤ንጹሕና፡ቅን፡ብትኾን፥
በእውነት፡አኹን፡ስለ፡አንተ፡ይነቃል፥
የጽድቅኽንም፡መኖሪያ፡ያከናውንልኻል።
7፤ዥማሬኽ፡ታናሽ፡ቢኾንም፡እንኳ፡
ፍጻሜኽ፡እጅግ፡ይበዛል።
8፤9፤ዘመናችን፡በምድር፡ላይ፡እንደ፡ጥላ፡ነውና፥
እኛ፡የትናንት፡ብቻ፡ነን፤ምንም፡አናውቅም፤
ስለዚህ፡የቀደመውን፡ትውልድ፡ጠይቅ፥
አባቶቻቸውም፡ለመረመሩት፡ነገር፡ትጋ፤
10፤እነርሱ፡የሚያስተምሩኽና፡የሚነግሩኽ፥
ቃልንም፡ከልባቸው፡የሚያወጡ፡አይደሉምን፧
11፤በእውኑ፡ደንገል፡ረግረግ፡በሌለበት፡መሬት፡ይበቅላልን፧
ወይስ፡ቄጠማ፡ውሃ፡በሌለበት፡ቦታ፡ይለመልማልን፧
12፤ገና፡ሲለመልም፡ሳይቈረጥም፥
ከአትክልት፡ዅሉ፡በፊት፡ይደርቃል።
13፤እግዚአብሔርን፡የሚረሱ፡ዅሉ፡ፍጻሜያቸው፡እንዲሁ፡ነው፤
የዝንጉም፡ሰው፡ተስፋ፡ይጠፋል።
14፤ተስፋው፡ይቈረጣል፥
እምነቱም፡እንደ፡ሸረሪት፡ቤት፡ይኾናል።
15፤ቤቱን፡ይደግፈዋል፥አይቆምለትም፤
ይይዘውማል፥አይጸናለትም።
16፤ፀሓይም፡ሳይተኵስ፡ይለመልማል፥
ጫፉም፡በአታክልቱ፡ቦታ፡ይወጣል።
17፤በድንጋይ፡ክምር፡ላይ፡ሥሩ፡ይጠመጠማል፤
የድንጋዮቹን፡ቦታ፡ይመለከታል።
18፤ከቦታው፡ቢጠፋ።
አላየኹኽም፡ብሎ፡ይክደዋል።
19፤እንሆ፥የመንገዱ፡ደስታ፡እንዲህ፡ነው፤
ሌላዎችም፡ከመሬት፡ይበቅላሉ።
20፤እንሆ፥እግዚአብሔር፡ፍጹሙን፡ሰው፡አይጥለውም፥
የኀጢአተኛዎችንም፡እጅ፡አያበረታም።
21፤አፍኽን፡እንደ፡ገና፡ሣቅ፡ይሞላል፥
ከንፈሮችኽንም፡እልልታ፡ይሞላል።
22፤የሚጠሉኽ፡ዕፍረት፡ይለብሳሉ፤
የኀጢአተኛዎችም፡ድንኳን፡አይገኝም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡9።______________
ምዕራፍ፡9።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤በእውነት፡እንዲህ፡እንደ፡ኾነ፡ዐወቅኹ፤
ሰውስ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ጻድቅ፡መኾን፡እንዴት፡ይችላል፧
3፤ከርሱ፡ጋራ፡ይከራከር፡ዘንድ፡ቢወድ፟፥
ከሺሕ፡ነገር፡አንዱን፡መመለስ፡አይችልም።
4፤ልቡ፡ጠቢብ፥ኀይሉም፡ታላቅ፡ነው፤
ደፍሮትስ፡በደኅና፡የኼደ፡ማን፡ነው፧
5፤ተራራዎችን፡ይነቅላል፤አያውቁትም፤
በቍጣውም፡ይገለብጣቸዋል።
6፤ምድርን፡ከስፍራው፡ያናውጣታል፥
ምሰሶዎቿም፡ይንቀጠቀጣሉ።
7፤ፀሓይን፡ያዛ፟ታል፥አትወጣምም፤
ከዋክብትንም፡ያትማል።
8፤ሰማያትን፡ብቻውን፡ይዘረጋል፥
በባሕሩም፡ማዕበል፡ላይ፡ይረግጣል።
9፤ድብ፡የሚባለውን፡ኮከብና፡ኦሪዮን፡የሚባለውን፡ኮከብ፥ሰባቱንም፡ከዋክብት፥
በደቡብም፡በኩል፡ያሉትን፡የከዋክብት፡ማደሪያዎች፡ሠርቷል።
10፤የማይመረመረውን፡ታላላቅ፡ነገር፥
የማይቈጠረውንም፡ተኣምራት፡ያደርጋል።
11፤እንሆ፥ቢመጣብኝ፡አላየውም፤
ቢያልፍብኝም፡አላውቀውም።
12፤እንሆ፥ፈጥኖ፡ቢነጥቅ፡የሚከለክለው፡ማን፡ነው፧
ርሱንስ፦ምን፡ታደርጋለኽ፧የሚለው፡ማን፡ነው፧
13፤እግዚአብሔር፡ቍጣውን፡አይመልስም፤
ከርሱ፡በታች፡ረዓብን፡የሚረዱ፡ይዋረዳሉ።
14፤ይልቁንስ፡እመልስለት፡ዘንድ፥
ቃሌንስ፡በፊቱ፡እመርጥ፡ዘንድ፡እኔ፡ማን፡ነኝ፧
15፤ጻድቅ፡ብኾን፡ኖሮ፡አልመልስለትም፡ነበር፤
ወደ፡ፈራጄም፡እለምን፡ነበር።
16፤ብጠራው፡ርሱም፡ቢመልስልኝ፡ኖሮ፥
ቃሌን፡እንደ፡ሰማ፡አላምንም፡ነበር።
17፤በዐውሎ፡ነፋስ፡ይሰብረኛል፥
ቍስሌንም፡ያለምክንያት፡ያበዛል።
18፤እተነፍስ፡ዘንድ፡አይተወኝም፥
ነገር፡ግን፡መራራን፡ነገር፡አጥግቦኛል።
19፤የኀይል፡ነገር፡ቢኾን፡ርሱ፡ኀያል፡ነው፤
የፍርድ፡ነገር፡ቢኾን፦ጊዜን፡ወሳኙ፡ማን፡ነው፧ይላል።
20፤ጻድቅ፡ብኾን፡አፌ፡ይወቅሰኛል፤
ፍጹምም፡ብኾን፡ጠማማ፡ያደርገኛል።
21፤ፍጹም፡ነኝ፡ራሴንም፡አልመለከትም፤
ሕይወቴንም፡እንቃታለኹ።
22፤ይህ፡ዅሉ፡አንድ፡ነው፤ስለዚህ፦
ፍጹማንንና፡ክፉዎችን፡ያጠፋል፡እላለኹ።
23፤መቅሠፍቱ፡ፈጥኖ፡ቢገድል፥
በንጹሓን፡ፈተና፡ይሳለቃል።
24፤ምድር፡በኃጥኣን፡እጅ፡ተሰጥታለች፤
የፈራጆቿን፡ፊት፡ሸፍኗል፤
ርሱ፡ካልኾነ፡ማን፡ነው፧
25፤ዘመኔ፡ከሚሮጥ፡ሰው፡ይልቅ፡ይፈጥናል፤
ይሸሻል፥መልካምንም፡አያይም።
26፤የደንገል፡ታንኳ፡እንደሚፈጥን፥
ንስርም፡ወደ፡ንጥቂያው፡እንደሚበር፟፡ያልፋል።
27፤እኔ፦የሐዘን፡እንጕርጕሮዬን፡እረሳለኹ፤
ፊቴን፡መልሼ፡እጽናናለኹ፡ብል፥
28፤ንጹሕ፡እንደማታደርገኝ፡እኔ፡ዐውቃለኹና፡
ከመከራዬ፡ዅሉ፡እፈራለኹ።
29፤በደለኛ፡እንደሚኾን፡ሰው፡እኾናለኹ፤
ስለ፡ምንስ፡በከንቱ፡እደክማለኹ፧
30፤በዐመዳይ፡ውስጥ፡ብታጠብ፥
እጆቼንም፡እጅግ፡ባነጻ፥
31፤በዐዘቅት፡ውስጥ፡ታሰጥመኛለኽ፥
ልብሴም፡ይጸየፈኛል።
32፤እንድመልስለት፡ዐብረን፡ወደ፡ፍርድ፡እንገባ፡ዘንድ፥
ርሱ፡እንደ፡እኔ፡ሰው፡አይደለም።
33፤እጁን፡በኹለታችን፡ላይ፡የሚያኖር፡ዳኛ፡
በመካከላችን፡ምነው፡በተገኘ!
34፤በትሩን፡ከእኔ፡ላይ፡ያርቅ፥
ግርማውም፡አያስፈራኝ፤
35፤እናገርም፡ነበር፥አልፈራውምም፡ነበር፤
በራሴ፡እንዲህ፡አይደለኹምና።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡10።______________
ምዕራፍ፡10።
1፤ነፍሴ፡ሕይወቴን፡ሰለቸቻት፤
የሐዘን፡እንጕርጕሮዬን፡እለቀዋለኹ፤
በነፍሴም፡ምሬት፡እናገራለኹ።
2፤እግዚአብሔርን፡እንዲህ፡እለዋለኹ።
አትፍረድብኝ፤የምትከራከረኝ፡ለምን፡እንደ፡ኾነ፡ንገረኝ።
3፤ልታስጨንቅና፡የእጅኽን፡ሥራ፡ልትንቅ፡
የኃጥኣንንስ፡ምክር፡ልታበራ፡
ባንተ፡ዘንድ፡መልካም፡ነውን፧
4፤በእውኑ፡የሥጋ፡ዐይን፡አለኽን፧
ወይስ፡ሰው፡እንደሚያይ፡ታያለኽን፧
5፤6፤ወይስ፡ክፋቴን፡ትፈላለግ፡ዘንድ፥
ኀጢአቴንም፡ትመረምር፡ዘንድ፥
ዘመንኽ፡እንደ፡ሰው፡ዘመን፡ነውን፧
ወይስ፡ዓመታትኽ፡እንደ፡ሰው፡ዓመታት፡ናቸውን፧
7፤ከዚህም፡በላይ፡በደለኛ፡እንዳልኾንኹ፥
ከእጅኽም፡የሚያድን፡እንደሌለ፡አንተ፡ታውቃለኽ።
8፤እጅኽ፡ለወሰችኝ፥ሠራችኝም፤
ከዚያም፡በዃላ፡ዞረኽ፡ታጠፋኝ፡ዘንድ፡ፈለግኽ።
9፤እንደ፡ጭቃ፡አድርገኽ፡እንደ፡ለወስኸኝ፡ዐስብ፤
ወደ፡ትቢያም፡ትመልሰኛለኽን፧
10፤በእውኑ፡እንደ፡ወተት፡አላፈሰስኸኝምን፧
እንደ፡ርጎስ፡አላረጋኸኝምን፧
11፤ቍርበትና፡ሥጋ፡አለበስኸኝ፥
በዐጥንትና፡በዥማትም፡አጠነከርኸኝ።
12፤ሕይወትና፡ቸርነት፡አደረግኽልኝ፤
መጐብኘትኽም፡መንፈሴን፡ጠበቀች።
13፤እነዚህንም፡ነገሮች፡በልብኽ፡ውስጥ፡ሰወርኽ።
ይህ፡ዅሉ፡በዐሳብኽ፡እንዳለ፡ዐውቃለኹ።
14፤ኀጢአት፡ብሠራ፡አንተ፡ትመለከተኛለኽ፤
ከኀጢአቴም፡ንጹሕ፡አታደርገኝም።
15፤በደለኛ፡ብኾን፡ወዮልኝ፤
ጻድቅም፡ብኾን፡ራሴን፡አላነሣም፤
ጕስቍልናን፡ተሞልቻለኹ፥
መከራዬንም፡ተመልክቻለኹ።
16፤ራሴም፡ከፍ፡ከፍ፡ቢል፡እንደ፡አንበሳ፡ታድነኛለኽ፤
ተመልሰኽም፡ድንቅ፡ነገር፡ታደርግብኛለኽ፡
17፤ምስክሮችኽን፡ታድስብኛለኽ፤
ቍጣኽንም፡ታበዛብኛለኽ፤
ጭፍራ፡በጭፍራ፡ላይ፡ትጨምርብኛለኽ።
18፤ስለ፡ምን፡ከማሕፀን፡አወጣኸኝ፧
ዐይን፡ሳያየኝ፡ምነው፡በሞትኹ።
19፤እንዳልነበረ፡በኾንኹ፤
ከማሕፀንም፡ወደ፡መቃብር፡በወሰዱኝ።
20፤የሕይወቴ፡ዘመን፡ጥቂት፡አይደለምን፧
21፤ወደማልመለስበት፡ስፍራ፥
ወደ፡ጨለማና፡ወደሞት፡ጥላ፡ምድር፥
22፤እንደ፡ጨለማም፡ወደጨለመች፥
ሥርዐትም፡ወደሌለባት፡ወደሞት፡ጥላ፥
ብርሃኗም፡እንደ፡ጨለማ፡ወደ፡ኾነ፡ምድር፡ሳልኼድ፥
ጥቂት፡እጽናና፡ዘንድ፡ተወኝ፥ልቀቀኝም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡11።______________
ምዕራፍ፡11።
1፤ነዕማታዊውም፡ሶፋር፡መለሰ፥እንዲህም፡አለ፦
2፤በእውኑ፡ለቃል፡ብዛት፡መልስ፡መስጠት፡አይገ፟ባ፟ምን፧
ወይስ፡ተናጋሪ፡ሰው፡እንደ፡ጻድቅ፡ይቈጠራልን፧
3፤ትምክሕትኽስ፡ሰዎችን፡ዝም፡ያሠኛቸዋልን፧
ብትሳለቅስ፡የሚያሳፍርኽ፡የለምን፧
4፤አንተ፦ትምህርቴ፡የተጣራ፡ነው፥
በዐይንኽም፡ፊት፡ንጹሕ፡ነኝ፡ትላለኽ።
5፤ምነው፡እግዚአብሔር፡ቢናገርኽ!
ባንተም፡ላይ፡ከንፈሩን፡ቢከፍት!
6፤የጥበቡን፡ምስጢር፡ቢገልጥልኽ!
ማስተዋሉ፡ብዙ፡ነውና።
እግዚአብሔር፡ለበደልኽ፡ከሚገ፟ባ፟ው፡አሳንሶ፡እንደሚያስከፍልኽ፡ዕወቅ።
7፤የእግዚአብሔርን፡ጥልቅ፡ነገር፡ልትመረምር፡ትችላለኽን፧
ወይስ፡ዅሉን፡የሚችል፡አምላክ፡ፈጽመኽ፡ልትመረምር፡ትችላለኽን፧
8፤ከሰማይ፡ይልቅ፡ከፍ፡ይላል፤ምን፡ልታደርግ፡ትችላለኽ፧
ከሲኦልም፡ይልቅ፡ይጠልቃል፤ምን፡ልታውቅ፡ትችላለኽ፧
9፤ርዝመቱ፡ከምድር፡ይልቅ፡ይረዝማል፥
ከባሕርም፡ይልቅ፡ይሰፋል።
10፤ርሱ፡ቢያልፍ፥ቢዘጋም፥ጉባኤንም፡ቢሰበስብ፥
የሚከለክለው፡ማን፡ነው፧
11፤ምናምንቴዎችን፡ሰዎች፡ያውቃልና፥
በደልንም፡ሲያይ፡ዝም፡ብሎ፡አይመለከትም።
12፤የሜዳ፡አህያ፡ግልገል፡ሰው፡ኾኖ፡ቢወለድ፥
ያን፡ጊዜ፡ከንቱ፡ሰው፡ጥበብን፡ያገኛል።
13፤14፤በእጅኽ፡በደል፡ቢኖር፡አርቀው፤
በድንኳንኽም፡ኀጢአት፡አይኑር፤
አንተ፡ልብኽን፡ቅን፡ብታደርግ፥
እጅኽንም፡ወደ፡ርሱ፡ብትዘረጋ፥
15፤በዚያን፡ጊዜ፡በእውነት፡ፊትኽን፡ያለነውር፡ታነሣለኽ፤
ትበረታለኽ፥አትፈራምም።
16፤መከራኽንም፡ትረሳለኽ፤
እንዳለፈ፡ውሃ፡ታስበዋለኽ።
17፤ከቅትር፡ይልቅ፡ሕይወትኽ፡ይበራል፤
ጨለማም፡ቢኾን፡እንደ፡ጧት፡ይኾናል።
18፤ተስፋም፡ስለ፡አለኽ፡ተዘልለኽ፡ትቀመጣለኽ፤
በዙሪያኽ፡ትመለከታለኽ፥በደኅንነትም፡ታርፋለኽ።
19፤ትተኛለኽ፥የሚያስፈራኽም፡የለም፤
ብዙ፡ሰዎችም፡ልመና፡ያቀርቡልኻል።
20፤የክፉዎች፡ዐይን፡ግን፡ትጨልማለች፤
የሚሸሹበትንም፡ያጣሉ፥
ተስፋቸውም፡ነፍሳቸውን፡ማውጣት፡ነው።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡12።______________
ምዕራፍ፡12።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤በርግጥ፡እናንተ፡ዐይነተኛዎች፡ሰዎች፡ናችኹ፤
ጥበብም፡ከእናንተ፡ጋራ፡ይሞታል።
3፤ነገር፡ግን፥እኔ፡ደግሞ፡እንደናንተ፡ማስተዋል፡አለኝ፤
ከእናንተም፡የማንስ፡አይደለኹም፤
እንደዚህ፡ያለውን፡ነገር፡የማያውቅ፡ማን፡ነው፧
4፤እግዚአብሔርን፡የጠራኹ፡ርሱም፡የመለሰልኝ፡እኔ፡
ለባልንጀራው፡መሳለቂያ፡እንደሚኾን፡ሰው፡ኾኛለኹ፤
ጻድቅና፡ፍጹም፡ሰው፡መሳለቂያ፡ኾኗል።
5፤ተዘልሎ፡በሚቀመጥ፡ሰው፡ዐሳብ፡መከራ፡ይናቃል፤
ነገር፡ግን፡እግሩን፡ሊያድጠው፡ተዘጋጅቷል።
6፤የቀማኛዎች፡ድንኳን፡በደኅንነት፡ይኖራል፥
እግዚአብሔርንም፡የሚያስቈጡ፡ተዘልለው፡ተቀምጠዋል፤
እግዚአብሔር፡ዅሉን፡በእጃቸው፡አምጥቶላቸዋል።
7፤አኹን፡ግን፡እንስሳዎችን፡ጠይቅ፥ያስተምሩኽማል፤
የሰማይንም፡ወፎች፡ጠይቅ፥ይነግሩኽማል።
8፤ወይም፡ለምድር፡ተናገር፥ርሷም፡ታስተምርኻለች፤
የባሕርም፡ዓሣዎች፡ይነግሩኻል።
9፤የእግዚአብሔር፡እጅ፡ይህን፡እንዳደረገ፡
ከነዚህ፡ዅሉ፡የማያውቅ፡ማን፡ነው፧
10፤የሕያዋን፡ዅሉ፡ነፍስ፡
የሰውም፡ዅሉ፡መንፈስ፡በእጁ፡ናት።
11፤ምላስ፡መብልን፡እንደሚቀምስ፥
ዦሮ፡ቃልን፡የሚለይ፡አይደለምን፧
12፤በሽምግልና፡ጊዜ፡ጥበብ፥
በዘመንስ፡ርዝመት፡ማስተዋል፡ይገኛል።
13፤በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ጥበብና፡ኀይል፡አለ፤
ለርሱ፡ምክርና፡ማስተዋል፡አለው።
14፤እንሆ፥ይፈርሳል፥የፈረሰውም፡ተመልሶ፡አይሠራም፤
በሰውም፡ቢዘጋበት፡የሚከፍትለት፡የለም።
15፤እንሆ፥ውሃዎቹን፡ይከለክላል፥እነርሱም፡ይደርቃሉ፤
እንደ፡ገና፡ይሰዳ፟ቸዋል፥ምድሪቱንም፡ይገለብጣሉ።
16፤ኀይልና፡ጥበብ፡በርሱ፡ዘንድ፡ናቸው፤
የሚስተውና፡የሚያስተው፡ለርሱ፡ናቸው።
17፤መካሮችንም፡እንደ፡ዘረፋ፡ይወስዳቸዋል፥
ፈራጆችንም፡ያሳብዳል።
18፤የነገሥታትንም፡እስራት፡ይፈታል፥
ወገባቸውንም፡በመታጠቂያ፡ያስራቸዋል።
19፤ካህናትን፡እንደ፡ዘረፋ፡ይወስዳቸዋል፥
ኀያላንንም፡ይገለብጣቸዋል።
20፤ከታመኑ፡ሰዎችም፡ቋንቋን፡ያርቃል፥
የሽማግሌዎችንም፡ማስተዋል፡ይወስድባቸዋል።
21፤በአለቃዎች፡ላይ፡ንቀትን፡ያፈሳ፟ል፥
የብርቱዎችንም፡መታጠቂያ፡ያላላል።
22፤ጥልቅ፡ነገር፡ከጨለማ፡ይገልጣል፥
የሞትንም፡ጥላ፡ወደ፡ብርሃን፡ያወጣል።
23፤አሕዛብን፡ከፍ፡ከፍ፡ያደርጋል፥እነርሱንም፡ያጠፋል፤
አሕዛብንም፡ያሰፋል፥እነርሱንም፡ያፈልሳቸዋል።
24፤ከምድር፡አሕዛብ፡አለቃዎች፡ዘንድ፡ማስተዋልን፡ይወስዳል፥
መንገድም፡በሌለበት፡በረሓ፡ያቅበዘብዛቸዋል።
25፤ብርሃንም፡ሳይኖር፡በጨለማ፡ይርመሰመሳሉ፤
እንደ፡ሰካራም፡ይቅበዘበዛሉ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡13።______________
ምዕራፍ፡13።
1፤እንሆ፥ይህን፡ዅሉ፡ዐይኔ፡አየች፤
ዦሮዬም፡ሰምታ፡አስተዋለችው።
2፤እናንተ፡የምታውቁትን፡እኔ፡ደግሞ፡ዐውቃለኹ፤
ከእናንተ፡የማንስ፡አይደለኹም።
3፤ነገር፡ግን፥ዅሉን፡ለሚችል፡አምላክ፡መናገር፡እፈልጋለኹ፥
ከእግዚአብሔርም፡ጋራ፡ለመዋቀስ፡እሻለኹ።
4፤እናንተ፡ግን፡በሐሰት፡ለባጮች፡ናችኹ፤
ዅላችኹ፡የማትጠቅሙ፡ባለመድኀኒቶች፡ናችኹ።
5፤ምነው፡ዝም፡ብላችኹ፡ብትኖሩ!
ይህ፡ጥበብ፡በኾነላችኹ፡ነበር።
6፤አኹንም፡ክርክሬን፡ስሙ፥
የከንፈሬንም፡ሙግት፡አድምጡ።
7፤በእውኑ፡ስለ፡እግዚአብሔር፡ሐሰትን፡ትናገራላችኹን፧
ስለ፡ርሱም፡ሽንገላን፡ታወራላችኹን፧
8፤ለፊቱስ፡ታደላላችኹን፧
ስለ፡እግዚአብሔርስ፡ትከራከራላችኹን፧
9፤ቢመረምራችኹስ፡መልካም፡ይኾንላችዃልን፧
ወይስ፡በሰው፡እንደምትሣለቁ፡ትሣለቁበታላችኹን፧
10፤በስውር፡ለሰው፡ፊት፡ብታደሉ፡
ዘለፋ፡ይዘልፋችዃል።
11፤ክብሩስ፡አያስፈራችኹምን፧
ግርማውስ፡አይወድቅባችኹምን፧
12፤ምስሌዎቻችኹ፡የዐመድ፡ምሳሌዎች፡ናቸው፤
ምሽጎቻችኹ፡የጭቃ፡ምሽጎች፡ናቸው።
13፤ዝም፡በሉ፥እናገርም፡ዘንድ፡ተዉኝ፤
የኾነው፡ነገር፡ይምጣብኝ።
14፤ሥጋዬን፡በጥርሴ፡እይዛለኹ፥
ሕይወቴንም፡በእጄ፡አኖራለኹ።
15፤እንሆ፥ቢገድለኝ፡ስንኳ፡ርሱን፡በትዕግሥት፡እጠባበቃለኹ፤
ነገር፡ግን፡መንገዴን፡በፊቱ፡አጸናለኹ።
16፤ዝንጉ፡ሰው፡በፊቱ፡አይገባምና፡
ርሱ፡መድኀኒት፡ይኾንልኛል።
17፤ነገሬን፡ተግታችኹ፡ስሙ፥
ምስክርነቴንም፡በዦሯችኹ፡አድምጡ።
18፤እንሆ፥ሙግቴን፡አዘጋጅቻለኹ።
እንደምጸድቅም፡ዐውቃለኹ።
19፤ከእኔስ፡ጋራ፡የሚፋረድ፡ማን፡ነው፧
አኹን፡እኔ፡ዝም፡ብል፡እሞታለኹ።
20፤ነገር፡ግን፥ኹለት፡ነገር፡አታድርግብኝ፤
የዚያን፡ጊዜ፡ከፊትኽ፡አልሰወርም፤
21፤እጅኽን፡ከእኔ፡አርቅ፤
ግርማኽም፡አታስደንግጠኝ።
22፤ከዚያም፡በዃላ፡ጥራኝ፥እኔም፡እመልስልኻለኹ።
ወይም፡እኔ፡ልናገር፥አንተም፡መልስልኝ።
23፤ያለብኝስ፡በደልና፡ኀጢአት፡ምን፡ያኽል፡ነው፧
መተላለፌንና፡ኀጢአቴን፡አስታውቀኝ።
24፤ፊትኽን፡ከእኔ፡የሰወርኽ፥
እንደ፡ጠላትኽም፡የቈጠርኸኝ፡ስለ፡ምን፡ነው፧
25፤የረገፈውን፡ቅጠል፡ታስጨንቃለኽን፧
ወይስ፡የደረቀውን፡ዕብቅ፡ታሳድዳለኽን፧
26፤የመረረ፡ነገር፡ጽፈኽብኛልና፤
የሕፃንነቴንም፡ኀጢአት፡ታወርሰኛለኽ።
27፤እግሬንም፡በእግር፡ግንድ፡አግብተኻል፥
መንገዴንም፡ዅሉ፡መርምረኻል፤
የእግሬን፡ፍለጋ፡ወስነኻል።
28፤እኔ፡እንደሚጠፋ፡በስባሳ፡ነገር፥
ብልም፡እንደሚበላው፡ልብስ፡ነኝ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡14።______________
ምዕራፍ፡14።
1፤ከሴት፡የተወለደ፡ሰው፡
የሕይወቱ፡ዘመን፡ጥቂት፡ቀን፡ነው፥መከራም፡ይሞላዋል።
2፤እንደ፡አበባ፡ይወጣል፥ይረግፋልም፤
እንደ፡ጥላም፡ይሸሻል፥ርሱም፡አይጸናም።
3፤እንደዚህስ፡ባለ፡ሰው፡ላይ፡ዐይኖችኽን፡ትከፍታለኽን፧
ከአንተስ፡ጋራ፡እኔን፡ወደ፡ፍርድ፡ታገባለኽን፧
4፤ከርኩስ፡ነገር፡ንጹሕን፡ሊያወጣ፡ማን፡ይችላል፧
አንድ፡እንኳ፡የሚችል፡የለም።
5፤የሰው፡ዕድሜ፡የተወሰነ፡ነው፥
የወሩም፡ቍጥር፡ባንተ፡ዘንድ፡ነው፥
ርሱም፡ሊተላለፈው፡የማይችለውን፡ዳርቻ፡አደረግኽለት።
6፤እንደ፡ምንደኛ፡ዕድሜው፡እስኪፈጸም፡ድረስ፡
ያርፍ፡ዘንድ፡ከርሱ፡ጥቂት፡ዘወር፡በል።
7፤ዛፍ፡ቢቈረጥ፡ደግሞ፡ያቈጠቍጥ፡ዘንድ፥
ቅርንጫፉም፡እንዳያልቅ፡ተስፋ፡አለው።
8፤ሥሩም፡በምድር፡ውስጥ፡ቢያረጅ፥
ግንዱም፡በመሬት፡ውስጥ፡ቢሞት፥
9፤ከውሃ፡ሽታ፡የተነሣ፡ያቈጠቍጣል፤
እንደ፡አትክልት፡ቅርንጫፍ፡ያወጣል።
10፤ሰው፡ግን፡ይሞትና፡ይጋደማል፤
ሰውም፡ነፍሱን፡ይሰጣል፥ርሱስ፡ወዴት፡አለ፧
11፤ውሃ፡ከባሕር፡ውስጥ፡ያልቃል፤
ወንዙም፡ያንሳል፡ይደርቅማል።
12፤ሰውም፡ተኝቶ፡አይነሣም፤
ሰማይ፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡አይነቃም፥
ከእንቅልፉም፡አይነሣም።
13፤በሲኦል፡ውስጥ፡ምነው፡በሰወርኸኝ፡ኖሮ!
ቍጣኽ፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡በሸሸግኸኝ፡ኖሮ!
ቀጠሮም፡አድርገኽ፡ምነው፡ባሰብኸኝ፡ኖሮ!
14፤በእውኑ፡ሰው፡ከሞተ፡ተመልሶ፡ሕያው፡ይኾናልን፧
መለወጤ፡እስኪመጣ፡ድረስ፥
የሰልፌን፡ዘመን፡ዅሉ፡በትዕግሥት፡በተጠባበቅኹ፡ነበር።
15፤በጠራኸኝና፡በመለስኹልኽ፡ነበር፤
የእጅኽንም፡ሥራ፡በተመኘኸው፡ነበር።
16፤አኹን፡ግን፡ርምጃዬን፡ቈጥረኸዋል፤
ኀጢአቴንም፡ትጠባበቃለኽ።
17፤መተላልፌ፡በከረጢት፡ውስጥ፡ታትሟል፥
ኀጢአቴንም፡ለብጠኽበታል።
18፤ተራራ፡ሲወድቅ፡ይጠፋል፥
አለቱም፡ከስፍራው፡ይፈልሳል፤
19፤ውሃዎች፡ድንጋዮቹን፡ይፍቃሉ፤
ፈሳሾቹም፡የምድሩን፡ዐፈር፡ይወስዳሉ፤
እንዲሁ፡የሰውን፡ተስፋ፡ታጠፋዋለኽ።
20፤ለዘለዓለም፡ታሸንፈዋለኽ፥ርሱም፡ያልፋል፤
ፊቱን፡ትለውጣለኽ፥ርሱንም፡ትሰደ፟ዋለኽ።
21፤ልጆቹ፡ቢከብሩ፡አያውቅም፤
ቢዋረዱም፡አያይም።
22፤ነገር፡ግን፥የገዛ፡ሥጋው፡ሕመም፡ብቻ፡ይሰማዋል፥
ለራሱም፡ብቻ፡ያለቅሳል።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡15።______________
ምዕራፍ፡15።
1፤ቴማናዊውም፡ኤልፋዝ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤በእውኑ፡ጠቢብ፡ሰው፡እንደ፡ነፋስ፡በኾነ፡ዕውቀት፡ይመልሳልን፧
በሆዱስ፡የምሥራቅን፡ነፋስ፡ይሞላልን፧
3፤ከማይረባ፡ነገር፥
ወይስ፡ከማይጠቅም፡ንግግር፡ጋራ፡ይዋቀሳልን፧
4፤አንተም፡እግዚአብሔርን፡መፍራት፡ታፈርሳለኽ፤
በእግዚአብሔር፡ፊት፡አምልኮን፡ታስቀራለኽ።
5፤በደልኽ፡አፍኽን፡ያስተምረዋል፥
የተንኰለኛዎችንም፡አንደበት፡ትመርጣለኽ።
6፤የሚፈርድብኽ፡አፍኽ፡ነው፡እንጂ፡እኔ፡አይደለኹም።
ከንፈሮችኽም፡ይመሰክሩብኻል።
7፤በእውኑ፡መዠመሪያ፡የተወለድኽ፡ሰው፡አንተ፡ነኽን፧
ወይስ፡ከተራራዎች፡በፊት፡ተፀነስኽን፧
8፤የእግዚአብሔርንስ፡ምስጢር፡ሰምተኻልን፧
ወይስ፡ጥበብን፡ለብቻኽ፡አድርገኻልን፧
9፤እኛ፡የማናውቀውን፡አንተ፡የምታወቀው፡ምንድር፡ነው፧
ከእኛ፡ዘንድስ፡የሌለው፡የምታስተውለው፡ምንድር፡ነው፧
10፤በዕድሜ፡ከአባትኽ፡የሚበልጡ፡
ሽበትም፡ያላቸው፡ሽማግሌዎችም፡ከእኛ፡ጋራ፡አሉ።
11፤በእውኑ፡የእግዚአብሔር፡ማጽናናት፥
በየውሀትም፡የተነገረኽ፡ቃል፡ጥቂት፡ነውን፧
12፤ልብኽስ፡ለምን፡ይወስድኻል፧
ዐይኖችኽስ፡ለምን፡ይገለምጣሉ፧
13፤በእግዚአብሔር፡ላይ፡መንፈስኽን፡እስከ፡ማንሣት፡ደርሰኽ፤
ይህንም፡ቃል፡ከአፍኽ፡እስከ፡ማውጣት፡ደርሰኽ።
14፤ንጹሕ፡ይኾን፡ዘንድ፡ሰው፡ምንድር፡ነው፧
ጻድቅስ፡ይኾን፡ዘንድ፡ከሴት፡የተወለደ፡ምንድር፡ነው፧
15፤እንሆ፥በቅዱሳኑ፡ስንኳ፡አይታመንም፤
ሰማያትም፡በፊቱ፡ንጹሓን፡አይደሉም።
16፤ይልቁንስ፡አስጸያፊና፡የረከሰ፥
ኀጢአትንም፡እንደ፡ውሃ፡የሚጠጣ፡ሰው፡ምንኛ፡ያንስ፧
17፤18፤ምድሪቱ፡ለብቻቸው፡ተሰጥታ፡የነበር፥
19፤በመካከላቸውም፡እንግዳ፡ያልገባባቸው፡ጠቢባን።
ከአባቶቻቸው፡ተቀብለው፡የተናገሩትን፡ያልሸሸጉትንም፥
እገልጥልኻለኹ፥ስማኝ፤ያየኹትንም፡እነግርኻለኹ።
20፤ክፉ፡ሰው፡ዕድሜውን፡ሙሉ፥
ከግፈኛ፡በተመደቡለት፡በዓመታት፡ዅሉ፡በሕመም፡ይጣጣራል።
21፤የሚያስደነግጥ፡ድምፅ፡በዦሮው፡ነው፤
በደኅንነቱም፡ሳለ፡ቀማኛ፡ይመጣበታል።
22፤ከጨለማ፡ተመልሶ፡እንዲወጣ፡አያምንም፥
ሰይፍም፡ይሸምቅበታል።
23፤ተቅበዝብዞም፦ወዴት፡አለ፧እያለ፡እንጀራ፡ይለምናል፤
የጨለማ፡ቀን፡እንደ፡ቀረበበት፡ያውቃል።
24፤መከራና፡ጭንቀት፡ያስፈራሩታል፤
ለሰልፍ፡እንደ፡ተዘጋጀ፡ንጉሥ፡ያሸንፉታል፤
25፤እጁን፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ዘርግቷልና፥
ዅሉንም፡በሚችል፡አምላክ፡ላይ፡ደፍሯልና፥
26፤በደንዳና፡ዐንገቱና፡በወፍራሙ፡በጋሻው፡
ጕብጕብ፡እየሰገገ፡ይመጣበታልና፥
27፤በስብም፡ፊቱን፡ከድኗልና፥
ስቡንም፡በወገቡ፡ላይ፡አድርጓልና፥
28፤በተፈቱም፡ከተማዎች፡ውስጥ፥
ሰውም፡በሌለባቸው፥
ክምር፡ለመኾን፡በተመደቡ፡ቤቶች፡ውስጥ፡ተቀምጧልና፥
29፤ባለጠጋ፡አይኾንም፥ሀብቱም፡አይጸናም፤
ጥላውንም፡በምድር፡ላይ፡አይጥልም፤
30፤ከጨለማ፡አይወጣም፤
ነበልባሉም፡ቅርንጫፎቹን፡ያደርቃቸዋል፥
አበባዎቹም፡ይረግፋሉ።
31፤ዋጋው፡ከንቱ፡ነገር፡ይኾናልና፥
ራሱን፡እያሳተ፡በከንቱ፡ነገር፡አይታመን።
32፤ቀኑ፡ሳይደርስ፡ጊዜው፡ይፈጸማል፥
ቅርንጫፉም፡አይለመልምም።
33፤እንደ፡ወይን፡ያልበሰለውን፡ዘለላ፡ያረግፋል፤
እንደ፡ወይራ፡አበባውን፡ይጥላል።
34፤የዝንጉዎች፡ጉባኤ፡ዅሉ፡ለጥፋት፡ይኾናል፥
የጕቦ፡ተቀባዮችንም፡ድንኳን፡እሳት፡ትበላለች።
35፤ጕዳትን፡ይፀንሳሉ፥በደልንም፡ይወልዳሉ፥
ሆዳቸውም፡ተንኰልን፡ያዘጋጃል።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡16።______________
ምዕራፍ፡16።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤እንደዚህ፡ያለ፡ዐይነት፡ነገር፡እጅግ፡ሰማኹ፤
እናንተ፡ዅላችኹ፡የምታደክሙ፡አጽናኞች፡ናችኹ።
3፤በእውኑ፡ከንቱ፡ቃል፡ይፈጸማልን፧
ወይስ፡ትመልስ፡ዘንድ፡ያነሣሣኽ፡ምንድር፡ነው፧
4፤እኔ፡ደግሞ፡እንደናንተ፡እናገር፡ዘንድ፡ይቻለኝ፡ነበር፤
ነፍሳችኹ፡በነፍሴ፡ፋንታ፡ቢኾን፡ኖሮ፥
እኔ፡በእናንተ፡ላይ፡ቃል፡ማሳካት፥
ራሴንም፡በእናንተ፡ላይ፡መነቅነቅ፡በተቻለኝ፡ነበር።
5፤በአፌም፡ነገር፡ባበረታዃችኹ፡ነበር፤
የከንፈሬን፡ማጽናናት፡ባልከለከልኹም፡ነበር።
6፤እኔ፡ብናገር፡ሕማሜ፡አይቀነስም፤
ዝምም፡ብል፡ከእኔ፡አይወገድም።
7፤አኹን፡ግን፡አድክሞኛል፤
ወገኔንም፡ዅሉ፡አፍርሰኻል።
8፤መጨማተሬ፡ይመሰክርብኛል፤
ክሳቴም፡ተነሥቶብኛል፤
በፊቴም፡ይመሰክርብኛል።
9፤በቍጣው፡ቀደደኝ፥ርሱም፡ጠላኝ፤
ጥርሶቹንም፡አፋጨብኝ፤
ጠላቴ፡ዐይኑን፡አፈጠጠብኝ፤
10፤እነርሱም፡አፋቸውን፡ከፈቱብኝ፤
እያላገጡ፡ጕንጬን፡ጠፈጠፉኝ፤
በአንድነትም፡ተሰበሰቡብኝ።
11፤እግዚአብሔር፡ለጠማማ፡ሰው፡አሳልፎ፡ሰጠኝ፥
በክፉዎችም፡እጅ፡ጣለኝ።
12፤ተዘልዬ፡ተቀምጬ፡ነበር፥ርሱም፡ሰበረኝ፤
ዐንገቴንም፡ይዞ፡ቀጠቀጠኝ፤
እንደ፡ዐላማ፡አድርጎ፡አቆመኝ።
13፤ቀስተኛዎቹ፡ከበቡኝ፤
ኵላሊቴንም፡ቈራረጠ፥ርሱም፡አልራራም፤
ሐሞቴን፡በምድር፡ላይ፡አፈሰሰ።
14፤በቍስል፡ላይ፡ቍስል፡ጨመረብኝ፤
እንደ፡ኀያል፡እየሰገገ፡ይሮጥብኛል።
15፤በቍርበቴ፡ላይ፡ማቅ፡ሰፋኹ፥
ቀንዴንም፡በመሬት፡ላይ፡አኖርኹ።
16፤ፊቴ፡ከልቅሶ፡የተነሣ፡ቀላ፤
የሞት፡ጥላ፡በዐይኖቼ፡ቆብ፡ላይ፡አለ፤
17፤ነገር፡ግን፥በእጄ፡ዐመፅ፡የለም፤
ጸሎቴም፡ንጹሕ፡ነው።
18፤ምድር፡ሆይ፥ደሜን፡አትክደኚ፥
ለጩኸቴም፡ማረፊያ፡አይኹን።
19፤አኹንም፥እንሆ፥ምስክሬ፡በሰማይ፡አለ፥
የሚመሰክርልኝም፡በአርያም፡ነው።
20፤ጸሎቴ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ይድረስ፥
ዐይኔም፡በፊቱ፡እንባ፡ታፍስ፟።
21፤የሰው፡ልጅ፡ከባልንጀራው፡ጋራ፡እንደሚሟገት፥
ሰው፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለመሟገት፡ምነው፡በቻለ!
22፤ጥቂቶች፡ዓመታት፡ካለፉ፡በዃላ፡
እኔ፡ወደማልመለስበት፡መንገድ፡እኼዳለኹ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡17።______________
ምዕራፍ፡17።
1፤መንፈሴ፡ደከመ፥ዘመኔ፡አለቀ፥
መቃብርም፡ተዘጋጅቶልኛል።
2፤አላጋጮች፡በእኔ፡ዘንድ፡አሉ፥
ዐይኔም፡በማስቈጣታቸው፡ዐደረች።
3፤አኹንም፡አንተ፡መያዣ፡ኾነኽ፡ተዋሰኝ፤
ከእኔ፡ጋራ፡አጋና፡የሚመታ፡ማን፡ነው፧
4፤ልባቸውም፡እንዳያስተውል፡ከልክለኸዋል፤
ስለዚህ፡ከፍ፡ከፍ፡አታደርጋቸውም።
5፤ለብዝበዛ፡ባልንጀራዎቹን፡አሳልፎ፡የሚሰጥ፡ሰው፥
የልጆቹ፡ዐይን፡ይጨልማል።
6፤ለሕዝብም፡ምሳሌ፡አደረገኝ፤
በፊቱ፡ላይ፡ጺቅ፡እንደሚሉበት፡ሰው፡ኾንኹ።
7፤ዐይኔም፡ከሐዘን፡የተነሣ፡ፈዘዘች፥
ብልቶቼም፡ዅሉ፡እንደ፡ጥላ፡ኾኑ።
8፤ቅኖች፡ሰዎች፡በዚህ፡ነገር፡ይደነቃሉ፥
ንጹሕም፡በዝንጉው፡ላይ፡ይበሳጫል።
9፤ጻድቅ፡ግን፡መንገዱን፡ያጠነክራል፥
እጁም፡ንጹሕ፡የኾነ፡ሰው፡ኀይልን፡እየጨመረ፡ይኼዳል።
10፤ነገር፡ግን፥እናንተ፡ዅሉ፡ተመልሳችኹ፡ወደ፡እኔ፡ኑ፤
በእናንተም፡ዘንድ፡ብልኀተኛ፡አላገኝም።
11፤ዕድሜዬ፡ዐለፈች፤
ዐሳቤና፡የልቤ፡መሣሪያ፡ተቈረጠ።
12፤ሌሊቱን፡ወደ፡ቀን፡ይለውጣሉ፤
ብርሃኑም፡ወደ፡ጨለማ፡የቀረበ፡ይመስላቸዋል።
13፤ተስፋ፡ባደርግ፡ሲኦል፡ቤቴ፡ናት፤
ምንጣፌንም፡በጨለማ፡ዘርግቻለኹ።
14፤መበስበስን፦አንተ፡አባቴ፡ነኽ፤
ትልንም፦አንቺ፡እናቴ፣እኅቴም፡ነሽ፡ብያለኹ።
15፤እንግዲህ፡ተስፋዬ፡ወዴት፡ነው፧
ተስፋዬንስ፡የሚያይ፡ማን፡ነው፧
16፤ዐብረን፡በመሬት፡ውስጥ፡ስናርፍ፥
ወደ፡ሲኦል፡ይወርዳል።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡18።______________
ምዕራፍ፡18።
1፤ሹሐዊውም፡በልዳዶስ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤እስከ፡መቼ፡ቃልን፡ታጠምዳለኽ፧
አስተውል፥ከዚያም፡በዃላ፡እንናገራለን።
3፤ስለ፡ምንስ፡እንደ፡እንስሳዎች፡ተቈጠርን፧
ስለ፡ምንስ፡በዐይንኽ፡ፊት፡ረከስን፧
4፤ቍጣ፡ወርሶኻል፤አንተስ፡የሞትኽ፡እንደ፡ኾነ፥
ምድር፡ስለ፡አንተ፡ባድማ፡ትኾናለችን፧
ወይስ፡አለት፡ከስፍራው፡ይነቀላልን፧
5፤የኀጢአተኛ፡መብራት፡ይጠፋል፥
የእሳቱም፡ነበልባል፡ብልጭ፡አይልም።
6፤ብርሃን፡በድንኳኑ፡ውስጥ፡ይጨልማል፥
መብራቱም፡በላዩ፡ይጠፋል።
7፤የኀይሉም፡ርምጃ፡ትጠባ፟ለች፥
ምክሩም፡ትጥለዋለች።
8፤እግሩ፡በወጥመድ፡ትያዛለች፥
በመረብም፡ላይ፡ይኼዳል።
9፤አሽክላ፡ሰኰናውን፡ይይዛል፥
ወስፈንጠርም፡ይበረታበታል።
10፤በምድር፡ላይ፡የሸምቀቆ፡ገመድ፥
በመንገዱም፡ላይ፡ወጥመድ፡ለርሱ፡ተሰውራለች።
11፤ድንጋጤ፡በዙሪያው፡ታስፈራዋለች፥
በስተዃላውም፡ኾና፡ታባርራቸዋለች።
12፤ኀይሉ፡በራብ፡ትደክማለች፥
መቅሠፍትም፡እስኪሰናከል፡ተዘጋጅቶለታል።
13፤የሰውነቱ፡ብልቶች፡ይጠፋሉ፤
የሞትም፡በኵር፡ልጅ፡ብልቶቹን፡ይበላል።
14፤ከሚታመንበት፡ድንኳን፡ይነቀላል፤
ወደ፡ድንጋጤም፡ንጉሥ፡ያስቸኵሉታል።
15፤በድንኳኑ፡ውስጥ፡ለርሱ፡የማይኾነው፡ይኖራል፤
በመኖሪያውም፡ላይ፡ዲን፡ይበተናል።
16፤ሥሩ፡ከበታቹ፡ይደርቃል፥
ጫፉም፡ከበላይ፡ይረግፋል።
17፤መታሰቢያው፡ከምድር፡ላይ፡ይጠፋል፥
በሜዳም፡ስም፡አይቀርለትም።
18፤ከብርሃን፡ወደ፡ጨለማ፡ያፈልሱታል፥
ከዓለምም፡ያሳድዱታል።
19፤ዘርም፡ትውልድም፡በሕዝቡ፡መካከል፡አይኾንለትም፤
በመኖሪያውም፡ውስጥ፡የሚቀመጥ፡ሰው፡አይቀርለትም።
20፤የፊተኛዎች፡ሰዎች፡እንደ፡ደነገጡ፥
እንዲሁ፡የዃለኛዎች፡ሰዎች፡ስለ፡ዘመኑ፡ይደነቃሉ።
21፤በእውነት፡የኀጢአተኛዎች፡ቤት፡እንዲሁ፡ናት፥
እግዚአብሔርንም፡የማያውቅ፡ሰው፡ስፍራ፡ይህ፡ነው።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡19።______________
ምዕራፍ፡19።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ነፍሴን፡የምትነዘንዙ፥
በቃልስ፡የምታደቁ፟ኝ፡እስከ፡መቼ፡ነው፧
3፤ይኸው፡ስትሰድቡኝ፡ዐሥር፡ጊዜ፡ነው፤
ስታሻክሩኝም፡አላፈራችኹም።
4፤በእውነትም፡የሳትኹ፡እንደ፡ኾነ፥
ስሕተቴ፡ከእኔ፡ጋራ፡ትኖራለች።
5፤በእውነትም፡ብትጓደዱብኝ፥
መዋረዴን፡በእኔ፡ላይ፡ብትከራከሩ፥
6፤እንግዲህ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ገለበጠኝ፥
በመረቡም፡እንደ፡ከበበኝ፡ዕወቁ።
7፤እንሆ፥ስለተደረገብኝ፡ግፍ፡ብጮኽ፡ማንም፡አይመልስልኝም፤
አሰምቼም፡ብጠራ፡ፍርድ፡የለኝም።
8፤እንዳላልፍ፡መንገዴን፡ዘግቶታል፥
በጐዳናዬም፡ጨለማ፡አኑሮበታል።
9፤ክብሬን፡ገፈፈኝ፥
ዘውዴንም፡ከራሴ፡ላይ፡ወሰደ።
10፤በዚህና፡በዚያም፡አፈረሰኝ፥እኔም፡ኼድኹ፤
ተስፋዬንም፡እንደ፡ዛፍ፡ነቀለው፤
11፤ቍጣውንም፡አነደደብኝ፥
እንደ፡ጠላቱም፡ቈጠረኝ።
12፤ሰራዊቱ፡ዐብረው፡መጡ፥
መንገዳቸውንም፡በላዬ፡አዘጋጁ፥
በድንኳኔም፡ዙሪያ፡ሰፈሩ።
13፤ወንድሞቼን፡ከእኔ፡ዘንድ፡አራቀ፥
የሚያውቁኝም፡አጥብቀው፡ተለዩኝ።
14፤ዘመዶቼ፡ተቋረጡ፥
ወዳጆቼም፡ረሱኝ።
15፤ቤተ፡ሰቦቼና፡ሴቶች፡ባሪያዎቼ፡እንደ፡መጻተኛ፡ቈጠሩኝ፤
በዐይናቸውም፡እንደ፡እንግዳ፡ኾንኹ።
16፤ባሪያዬን፡ብጠራ፥በአፌም፡ባቈላምጥ፡አይመልስልኝም።
17፤ሚስቴ፡እስትንፋሴን፡ጠላች፥
የእናቴም፡ማሕፀን፡ልጆች፡ልመናዬን፡ጠሉ።
18፤ሕፃናት፡እንኳ፡አጠቁኝ፤
ብነሣም፡በእኔ፡ላይ፡ይናገራሉ።
19፤አማካሪዎቼ፡ዅሉ፡ተጸየፉኝ፤
እኔ፡የምወዳ፟ቸው፡በላዬ፡ተገለበጡ።
20፤ዐጥንቴ፡ከቍርበቴና፡ከሥጋዬ፡ጋራ፡ተጣበቀ፤
ድድ፡ብቻ፡ቀርቶልኝ፡አመለጥኹ።
21፤እናንተ፡ወዳጆቼ፡ሆይ፥ማሩኝ፤
የእግዚአብሔር፡እጅ፡መትታኛለችና፡ማሩኝ።
22፤ስለ፡ምን፡እናንተ፡እንደ፡እግዚአብሔር፡ታሳድዱኛላችኹ፧
ከሥጋዬስ፡ስለ፡ምን፡አትጠግቡም፧
23፤ምነው፡አኹን፡ቃሌ፡ቢጻፍ!
ምነው፡በመጽሐፍ፡ውስጥ፡ቢታተም!
24፤ምነው፡በብረት፡ብርና፡በርሳስ፡
በአለቱ፡ላይ፡ለዘለዓለም፡ቢቀረጽ!
25፤እኔን፡ግን፡የሚቤዠኝ፡ሕያው፡እንደ፡ኾነ፥
በመጨረሻም፡ዘመን፡በምድር፡ላይ፡እንዲቆም፥
26፤ይህ፡ቍርበቴም፡ከጠፋ፡በዃላ፥
በዚያን፡ጊዜ፡ከሥጋዬ፡ተለይቼ፡እግዚአብሔርን፡እንዳይ፡ዐውቃለኹ።
27፤እኔ፡ራሴ፡አየዋለኹ፥
ዐይኖቼም፡ይመለከቱታል፥
ከእኔም፡ሌላ፡አይደለም።
ልቤ፡በመናፈቅ፡ዝሏል።
28፤በእውነት፦እንዴት፡እናሳድደዋለን፧
የነገሩ፡ሥር፡በርሱ፡ዘንድ፡ተገኝቷል፡ብትሉ፥
29፤ፍርድ፡እንዳለ፡ታውቁ፡ዘንድ፡
ቍጣ፡የሰይፍን፡ቅጣት፡ያመጣልና፥
ከሰይፍ፡ፍሩ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡20።______________
ምዕራፍ፡20።
1፤ናዕማታዊውም፡ሶፋር፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ስለዚህ፥በውስጤ፡ስላለው፡ችኰላ፡ዐሳቤ፡ትመልስልኛለች።
3፤የሚያሳፍረኝንም፡ተግሣጽ፡ሰምቻለኹ፥
የማስተዋሌም፡መንፈስ፡ይመልስልኛል።
4፤ሰው፡በምድር፡ላይ፡ከተቀመጠ፥ከዱሮ፡ዘመን፡ዠምሮ፥
5፤የኀጢአተኛ፡ፉከራ፡ዐጪር፡መኾኑን፡
የዝንጉዎችም፡ደስታ፡ቅጽበት፡መኾኑን፡አታውቁምን፧
6፤ከፍታው፡ወደ፡ሰማይ፡ቢወጣ፥
ራሱም፡እስከ፡ደመና፡ቢደርስ፥
7፤እንደ፡ፋንድያ፡ለዘለዓለም፡ይጠፋል፤
ያዩትም፦ወዴት፡ነው፧ይላሉ።
8፤እንደ፡ሕልም፡ይበራ፟ል፥ርሱም፡አይገኝም፤
እንደ፡ሌሊትም፡ራእይ፡ይሰደዳል።
9፤ያየችውም፡ዐይን፡ዳግመኛ፡አታየውም፤
ስፍራውም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አይመለከተውም።
10፤ልጆቹ፡ድኻዎቹን፡ያቈላምጣሉ፤
እጁ፡ሀብቱን፡ይመልሳል።
11፤ዐጥንቶቹ፡ብላቴንነቱን፡ሞልተዋል፤
ነገር፡ግን፡ከርሱ፡ጋራ፡በመሬት፡ውስጥ፡ይተኛል።
12፤ክፋት፡በአፉ፡ውስጥ፡ቢጣፍጥ፥
ከምላሱም፡በታች፡ቢሰውረው፥
13፤ቢጠብቀውም፡ባይተወውም፥
በጕረሮውም፡ቢይዘው፥
14፤መብሉ፡በአንዠቱ፡ውስጥ፡ይገላበጣል፤
እንደ፡እፍኝትም፡ሐሞት፡በውስጡ፡ይኾናል።
15፤የዋጠውን፡ሀብት፡ይተፋዋል፤
እግዚአብሔርም፡ከሆዱ፡ውስጥ፡ያወጣዋል።
16፤የእፍኝትን፡መርዝ፡ይጠባል፤
የእባብም፡ምላስ፡ይገድለዋል።
17፤የማሩንና፡የቅቤውን፡ፈሳሽ፡
ወንዞቹንም፡አይመለከትም።
18፤የድካሙን፡ፍሬ፡ሳይውጠው፡ይመልሰዋል፤
እንደ፡ንግዱም፡ትርፍ፡አይደሰትም።
19፤ድኻውን፡አስጨንቋል፥ትቶታልም፤
ያልሠራውንም፡ቤት፡በዝብዟል።
20፤ሆዱ፡ዕረፍትን፡አላወቀምና፡
የወደደው፡ነገር፡አላዳነውም።
21፤ርሱ፡ከበላ፡በዃላ፡ምንም፡አልተረፈም፤
ስለዚህ፡በረከቱ፡አይከናወንለትም።
22፤በጠገበ፡ጊዜ፡ይጨነቃል፤
የችግረኛዎችም፡ዅሉ፡እጅ፡ታገኘዋለች።
23፤ሆዱን፡ሳያጠግብ፡
እግዚአብሔር፡የቍጣውን፡ትኵሳት፡ይሰድ፟በታል፥
ሲበላም፡ያዘንብበታል።
24፤ከብረት፡መሣሪያም፡ይሸሻል፥
የናስም፡ቀስት፡ይወጋዋል።
25፤ርሱም፡ይመዘ፟ዋል፥ከሥጋውም፡ይወጣል፤
ከሐሞቱም፡ብልጭ፡ብሎ፡ይሠርጻል፤
ፍርሀትም፡ይወድቅበታል።
26፤ጨለማ፡ዅሉ፡ስለከበረው፡ዕቃ፡ተዘጋጅቷል፤
በሰው፡አፍ፡እፍ፡የማትባል፡እሳት፡ትበላዋለች፤
በድንኳኑ፡ውስጥ፡የቀረው፡ይጨነቅባታል።
27፤ሰማይ፡ኀጢአቱን፡ይገልጥበታል፥
ምድርም፡ትነሣበታለች።
28፤የቤቱም፡ባለጠግነት፡ይኼዳል፤
በቍጣው፡ቀን፡እንደ፡ፈሳሽ፡ውሃ፡ያልፋል።
29፤ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የበደለኛ፡ሰው፡ዕድል፡ፈንታ፥
ከእግዚአብሔርም፡የተመደበ፡ርስቱ፡ይህ፡ነው።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡21።______________
ምዕራፍ፡21።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ስሙ፥ቃሌን፡ስሙ፤
ይህም፡መጽናናታችኹ፡ይኹን።
3፤እናገር፡ዘንድ፡ተዉኝ፤
ከተናገርኹም፡በዃላ፡ተሣለቁ።
4፤በእውኑ፡የሐዘን፡እንጉርጕሮዬ፡ለሰው፡እናገራለኹን፧
አለመታገሥ፡ስለ፡ምን፡አይገ፟ባ፟ኝም፧
5፤ወደ፡እኔ፡ተመልከቱ፥ተደነቁም፤
እጃችኹንም፡በአፋችኹ፡ላይ፡አኑሩ።
6፤እኔ፡ባሰብኹ፡ቍጥር፡እጨነቃለኹ፥
ጻዕርም፡ሥጋዬን፡ይይዛል።
7፤ስለ፡ምን፡ኀጢአተኛዎች፡በሕይወት፡ይኖራሉ፧
ስለ፡ምንስ፡ያረጃሉ፧በባለጠግነትስ፡ስለ፡ምን፡ይበረታሉ፧
8፤ዘራቸው፡ከነርሱ፡ጋራ፡ጸንቶ፡ይኖራል፥
ልጆቻቸውም፡በዐይናቸው፡ፊት፡ናቸው።
9፤ቤታቸው፡ከፍርሀት፡ወጥቶ፡የታመነ፡ነው፥
የእግዚአብሔርም፡በትር፡የለባቸውም።
10፤ኰርማቸው፡ይወልዳል፥ዘሩንም፡አይጥለውም፤
ላማቸውም፡ትወልዳለች፥አትጨነግፍም።
11፤ሕፃናታቸውን፡እንደ፡መንጋ፡ያወጣሉ፥
ልጆቻቸውም፡ይዘፍናሉ።
12፤ከበሮና፡መሰንቆ፡ወስደው፡ይዘምራሉ፥
በእንቢልታ፡ድምፅ፡ደስ፡ይላቸዋል።
13፤ዕድሜያቸውንም፡በተድላ፡ይፈጽማሉ፤
ድንገትም፡ወደ፡ሲኦል፡ይወርዳሉ።
14፤እግዚአብሔርንም፦ከእኛ፡ዘንድ፡ራቅ፤
መንገድኽን፡እናውቅ፡ዘንድ፡አንወድ፟ም።
15፤እናመልከውስ፡ዘንድ፡ዅሉን፡የሚችል፡አምላክ፡ማን፡ነው፧
ወይስ፡ወደ፡ርሱ፡ብንጸልይ፡ምን፡ይጠቅመናል፧ይላሉ።
16፤እንሆ፥ሀብታቸው፡በእጃቸው፡ውስጥ፡አይደለምን፧
የኃጥኣን፡ምክር፡ከእኔ፡ዘንድ፡የራቀች፡ናት።
17፤የኃጥኣን፡መብራት፡የጠፋው፥
መቅሠፍትም፡የመጣባቸው፥
እግዚአብሔርም፡በቍጣው፡መከራ፡የከፈላቸው፥
18፤በነፋስ፡ፊት፡እንደ፡ገለባ፥
ዐውሎ፡ነፋስም፡እንደሚወስደው፡ትቢያ፡የኾኑ፡ስንት፡ጊዜ፡ነው፧
19፤እናንተ፦እግዚአብሔር፡በደላቸውን፡ለልጆቻቸው፡ይጠብቃል፡ብላችዃል።
እነርሱ፡ያውቁ፡ዘንድ፡ፍዳን፡ለራሳቸው፡ይክፈል።
20፤ዐይኖቻቸው፡ጥፋታቸውን፡ይዩ፥
ዅሉን፡ከሚችል፡አምላክ፡ቍጣ፡ይጠጡ።
21፤የወራታቸውስ፡ቍጥር፡ቢቈረጥ፥
ከነርሱ፡በዃላ፡የቤታቸው፡ደስታ፡ምን፡ይኾናቸዋል፧
22፤ከፍ፡ከፍ፡ባሉትስ፡ላይ፡ለሚፈርድ፡ለእግዚአብሔር፡
በእውኑ፡ሰው፡ዕውቀትን፡ያስተምራልን፧
23፤አንድ፡ሰው፡በሰላም፡ተዘልሎ፡ሲቀመጥ፡
በሙሉ፡ኀይሉ፡ሳለ፡ይሞታል።
24፤በአንዠቱ፡ውስጥ፡ስብ፡ሞልቷል፥
የዐጥንቶቹም፡ቅልጥም፡ረጥቧል።
25፤ሌላውም፡ሰው፡መልካምን፡ነገር፡ከቶ፡ሳይቀምስ፡
በተመረረች፡ነፍስ፡ይሞታል።
26፤በዐፈር፡ውስጥ፡ባንድ፡ላይ፡ይተኛሉ፥
ትልም፡ይከድናቸዋል።
27፤እንሆ፥ዐሳባችኹን፥
የመከራችኹብኝንም፡ክፉ፡ምክር፡ዐውቄዋለኹ።
28፤እናንተ፦የከበርቴው፡ቤት፡የት፡ነው፧
ኀጢአተኛውም፡ያደረበት፡ድንኳን፡የት፡ነው፧ብላችዃል።
29፤መንገድ፡ዐላፊዎችን፡አልጠየቃችኹምን፧
ምልክታቸውን፡አታውቁምን፧
30፤ኀጢአተኛው፡በመቅሠፍት፡ቀን፡እንደ፡ተጠበቀ፥
በቍጣው፡ቀን፡እንደሚድን።
31፤መንገዱን፡በፊቱ፡የሚናገር፡ማን፡ነው፧
የሠራውንስ፡የሚመልስበት፡ማን፡ነው፧
32፤ርሱን፡ግን፡ወደ፡መቃብር፡ይሸከሙታል፥
ሰዎቹም፡በመቃብሩ፡ላይ፡ይጠብቃሉ።
33፤የሸለቆው፡ጓል፡ይጣፍጥለታል፤
በዃላውም፡ሰው፡ዅሉ፡ይሳባል፥
በፊቱም፡ቍጥር፡የሌለው፡ጉባኤ፡አለ።
34፤የምትመልሱልኝ፡ውስልትና፡ነውና፥
በከንቱ፡እንዴት፡ታጽናኑኛላችኹ፧
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡22።______________
ምዕራፍ፡22።
1፤ቴማናዊውም፡ኤልፋዝ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤በእውኑ፡ሰው፡እግዚአብሔርን፡ይጠቅመዋልን፧
በእውነት፡ጥበበኛ፡ሰው፡ራሱን፡ይጠቅማል።
3፤ጻድቅ፡መኾንኽስ፡ዅሉን፡የሚችለውን፡አምላክ፡ደስ፡ያሠኘዋልን፧
መንገድኽን፡ማቅናትኽስ፡ይጠቅመዋልን፧
4፤ርሱንስ፡ስለ፡ፈራኽ፡ይዘልፍኻልን፧
ወደ፡ፍርድስ፡ከአንተ፡ጋራ፡ይገባልን፧
5፤ክፋትኽስ፡የበዛ፡አይደለምን፧
ለኀጢአትኽም፡ፍጻሜ፡የላትም።
6፤የወንድሞችኽን፡መያዣ፡በከንቱ፡ወስደኻል፥
የዕርዝተኛዎቹንም፡ልብስ፡ዘርፈኻል።
7፤ለደካማ፡ውሃ፡አላጠጣኽም፥
ለራብተኛም፡እንጀራን፡ከልክለኻል።
8፤በክንድ፡የበረታ፡ምድርን፡ገዛ፤
ከበርቴውም፡ሰው፡ተቀመጠባት።
9፤መበለቲቱን፡አንዳች፡አልባ፡ሰደ፟ኻታል፤
የድኻ፡አደጎችም፡ክንድ፡ተሰብሯል።
10፤ስለዚህ፥አሽክላ፡ከቦ፟ኻል፥
ድንገተኛ፡ፍርሀትም፡አናውጦኻል።
11፤እንዳታይ፡ብርሃን፡ጨለማ፡ኾነችብኽ፥
የውሃዎችም፡ብዛት፡አሰጠመኽ።
12፤እግዚአብሔር፡በሰማያት፡ከፍ፡ከፍ፡አይልምን፧
ከዋክብትም፡እንዴት፡ከፍ፡ከፍ፡እንዳሉ፡ተመልከት።
13፤አንተም፦እግዚአብሔር፡ምን፡ያውቃል፧
በድቅድቅ፡ጨለማ፡ውስጥ፡ኾኖ፡ሊፈርድ፡ይችላልን፧
14፤እንዳያይ፡የጠቈረ፡ደመና፡ጋርዶታል፤
በሰማይ፡ክበብ፡ላይ፡ይራመዳል፡ብለኻል።
15፤በእውኑ፡ኀጢአተኛዎች፡ሰዎች፡የረገጧትን፡
የዱሮዪቱን፡መንገድ፡ትጠብቃለኽን፧
16፤ጊዜያቸው፡ሳይደርስ፡ተነጠቁ፤
መሠረታቸውም፡እንደ፡ፈሳሽ፡ውሃ፡ፈሰሰ።
17፤እግዚአብሔርንም፦ከእኛ፡ዘንድ፡ራቅ፤
ዅሉንም፡የሚችል፡አምላክ፡ምን፡ሊያደርግልን፡ይችላል፧አሉት።
18፤ነገር፡ግን፥ቤታቸውን፡በመልካም፡ነገር፡ሞላ፤
የኃጥኣን፡ምክር፡ከእኔ፡ዘንድ፡የራቀች፡ናት።
19፤ጻድቃን፡ያዩታል፥ደስም፡ይላቸዋል፤
ንጹሓንም፡በንቀት፡ይሥቁባቸዋል።
20፤በእውነት፡ሀብታቸው፡ጠፋ፥
የቀረውንም፡እሳት፡በላች።
21፤አኹንም፡ከርሱ፡ጋራ፡ተስማማ፥ሰላምም፡ይኑርኽ፤
በዚያም፡በጎነት፡ታገኛለኽ።
22፤ከአፉም፡ሕጉን፡ተቀበል፥
በልብኽም፡ቃሉን፡አኑር፤
23፤ዅሉን፡ወደሚችል፡አምላክ፡ብትመለስ፥ብትዋረድም፥
ኀጢአትንም፡ከድንኳንኽ፡ብታርቅ፥
24፤የወርቅን፡ዕቃ፡በዐፈር፡ውስጥ፥
የኦፊርንም፡ወርቅ፡በጅረት፡ድንጋይ፡መካከል፡ብትጥል፥
25፤ዅሉን፡የሚችል፡አምላክ፡ወርቅና፡የሚብለጨለጭ፡ብር፡ይኾንልኻል።
26፤የዚያን፡ጊዜ፡ዅሉን፡በሚችል፡አምላክ፡ደስ፡ይልኻል፥
ፊትኽንም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ታነሣለኽ።
27፤ወደ፡ርሱም፡ትጸልያለኽ፥ርሱም፡ይሰማኻል፤
ስእለትኽንም፡ትሰጣለኽ።
28፤ነገርንም፡ትመክራለኽ፥ርሱም፡ይሳካልኻል፤
ብርሃንም፡በመንገድኽ፡ላይ፡ይበራል።
29፤ቢያዋርዱኽ፡አንተ፡ከፍ፡ከፍ፡ትላለኽ፤
ትሑቱንም፡ሰው፡ያድነዋል።
30፤ንጹሑን፡ሰው፡ያድነዋል፤
በእጅኽም፡ንጽሕና፡ትድናለኽ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡23።______________
ምዕራፍ፡23።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ዛሬም፡ደግሞ፡የሐዘን፡እንጕርጕሮዬ፡ገና፡መራራ፡ነው፤
እጁ፡በልቅሶ፡ጩኸቴ፡ላይ፡ከብዳለች።
3፤ርሱን፡ወዴት፡እንዳገኘው፡ምነው፡ባወቅኹ!
ወደተቀመጠበትስ፡ስፍራ፡ምነው፡በደረስኹ!
4፤በፊቱ፡ሙግቴን፡አዘጋጅ፡ነበር፥
አፌንም፡በማስረጃ፡እሞላው፡ነበር።
5፤የሚመልስልኝም፡ቃል፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡ዐውቅ፡ነበር፥
የሚለኝንም፡አስተውል፡ነበር።
6፤በኀይሉ፡ብዛት፡ከእኔ፡ጋራ፡ይሟገት፡ነበርን፧
እንኳን! ያደምጠኝ፡ነበር።
7፤ቅን፡ሰው፡ከርሱ፡ጋራ፡በዚያ፡ይከራከር፡ነበር፤
እኔም፡ከፈራጄ፡ለዘለዓለም፡እድን፡ነበር።
8፤እንሆ፥ወደ፡ፊት፡እኼዳለኹ፥ርሱም፡የለም፤
ወደ፡ዃላም፡እኼዳለኹ፥እኔም፡አላስተውለውም፤
9፤ወደሚሠራበት፡ወደ፡ግራ፡ብኼድ፡አልመለከተውም፤
በቀኜም፡ይሰወራል፥አላየውምም፤
10፤የምኼድበትን፡መንገድ፡ያውቃል፤
ከፈተነኝም፡በዃላ፡እንደ፡ወርቅ፡እወጣለኹ።
11፤እግሬ፡ወደ፡ርምጃው፡ተጣብቋል፤
መንገዱንም፡ጠብቄያለኹ፥ፈቀቅም፡አላልኹም።
12፤ከከንፈሩ፡ትእዛዝ፡አልተመለስኹም፤
የአፉን፡ቃል፡በልቤ፡ሰውሬያለኹ።
13፤ርሱ፡ግን፡ብቻውን፡ነው፤ርሱንስ፡የሚመስለው፡ማን፡ነው፧
ነፍሱም፡የወደደችውን፡ያደርጋል።
14፤በእኔ፡ላይ፡የተወሰነውን፡ይፈጽማል፤
እንደዚህም፡ያለ፡ብዙ፡ነገር፡በርሱ፡ዘንድ፡አለ።
15፤ስለዚህ፥በፊቱ፡ደነገጥኹ፤
ባሰብኹም፡ጊዜ፡ከርሱ፡ፈራኹ።
16፤እግዚአብሔር፡ልቤን፡አባብቶታልና፥
ዅሉንም፡የሚችል፡አምላክ፡አስደንግጦኛል።
17፤ከጨለማው፡የተነሣ፥
ድቅድቁም፡ጨለማ፡ፊቴን፡ከመክደኑ፡የተነሣ፡አልደነገጥኹም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡24።______________
ምዕራፍ፡24።
1፤ዅሉን፡ከሚችል፡አምላክ፡ዘንድ፡ዘመናት፡አልተሰወረምና፡
ርሱን፡የሚያውቁ፡ለምን፡ወራቱን፡አያዩም፧
2፤የድንበሩን፡ምልክት፡የሚያፈርሱ፡አሉ፤
መንጋዎቹን፡በዝብዘው፡ያሰማራሉ።
3፤የድኻ፡አደጎቹን፡አህያ፡ይነዳሉ፤
የመበለቲቱን፡በሬ፡ስለ፡መያዣ፡ይወስዳሉ።
4፤ድኻዎቹን፡ከመንገዱ፡ያወጣሉ፤
የምድርም፡ችግረኛዎች፡ዅሉ፡ይሸሸጋሉ።
5፤እንሆ፥በምድረ፡በዳ፡እንዳሉ፡እንደ፡ሜዳ፡አህያዎች፥
መብልን፡ፈልገው፡ወደ፡ሥራቸው፡ይወጣሉ፤
ምድረ፡በዳውም፡ለልጆቻቸው፡መብልን፡ይሰጣቸዋል።
6፤እነዚያ፡በዕርሻ፡ውስጥ፡እኽላቸውን፡ያጭዳሉ፤
የበደለኛውንም፡ወይን፡ይቃርማሉ።
7፤ዕራቍታቸውን፡ያለልብስ፡ያድራሉ፥
በብርድ፡ጊዜ፡መጐናጸፊያ፡የላቸውም።
8፤ከተራራዎች፡በሚወርድ፡ዝናብ፡ይረጥባሉ፤
መጠጊያም፡ዐጥተው፡ቋጥኙን፡ያቅፋሉ።
9፤ድኻ፡አደጉን፡ልጅ፡ከጡቱ፡የሚነጥሉ፡አሉ፡
ከችግረኛውም፡መያዣ፡ይወስዳሉ።
10፤ያለ፡ልብስ፡ዕራቍታቸውን፡ይኼዳሉ፤
ተርበውም፡ነዶዎችን፡ይሸከማሉ፤
11፤በእነዚህ፡ሰዎች፡ዐጥር፡ውስጥ፡ዘይት፡ያደርጋሉ፤
ወይንም፡ይጠምቃሉ፥ነገር፡ግን፥ይጠማሉ።
12፤ከከተማውና፡ከገዛ፡ቤቶቻቸው፡ይባረራሉ፤
የልጆችም፡ነፍስ፡ለርዳታ፡ትጮኻለች፤
እግዚአብሔር፡ግን፡ስንፍናቸውን፡አይመለከትም።
13፤እነዚህ፡በብርሃን፡ላይ፡የሚያምፁ፡ናቸው፤
መንገዱን፡አያውቁም፥በጐዳናውም፡አይጸኑም።
14፤ነፍሰ፡ገዳዩም፡ሳይነጋ፡ማልዶ፡ይነሣል፤
ችግረኛዎችንና፡ድኻዎችን፡ይገድላል፤
በሌሊትም፡እንደ፡ሌባ፡ነው።
15፤የአመንዝራም፡ዐይን፡ድግዝግዝታን፡ይጠብቃል።
የማንም፡ዐይን፡አያየኝም፡ይላል፥
ፊቱንም፡ይሸፍናል።
16፤ቤቶቹን፡በጨለማ፡ይነድላሉ፤
በቀን፡ይሸሸጋሉ፤
ብርሃንም፡አያውቁም።
17፤የጧት፡ብርሃን፡ለእነርሱ፡ዅሉ፡እንደ፡ሞት፡ጥላ፡ነው፤
የሞትን፡ጥላ፡ድንጋጤ፡ያውቃሉና።
18፤እነርሱ፡በውሃ፡ፊት፡ላይ፡በረ፟ው፡ያልፋሉ፤
ዕድል፡ፈንታቸውም፡በምድር፡ላይ፡የተረገመች፡ናት፤
ወደ፡ወይኑ፡ቦታ፡መንገድ፡አይዞሩም።
19፤ድርቅና፡ሙቀት፡የዐመዳዩን፡ውሃ፡ያጠፋሉ፤
እንዲሁ፡ሲኦል፡በደለኛዎችን፡ታጠፋለች።
20፤ማሕፀን፡ትረሳዋለች፤
ትልም፡በደስታ፡ይጠባዋል፤
ዳግመኛም፡አይታሰብም፤
ክፋትም፡እንደ፡ዛፍ፡ይሰበራል።
21፤የማትወልደውን፡መካኒቱን፡ይበድላታል፤
ለመበለቲቱም፡በጎነት፡አያደርግም።
22፤ነገር፡ግን፥በኀይሉ፡ኀያላንን፡ይስባል፤
ርሱም፡በተነሣ፡ጊዜ፡ሰው፡በሕይወቱ፡አይታመንም።
23፤እግዚአብሔር፡በደኅና፡አኑሯቸዋል፥
በዚያም፡ይታመናሉ፤
ዐይኖቹ፡ግን፡በመንገዳቸው፡ላይ፡ናቸው።
24፤ጥቂት፡ጊዜ፡ከፍ፡ከፍ፡ይላሉ፤
ይኼዳሉ፥ይጠወልጋሉም፤
እንደ፡ሌላዎች፡ዅሉ፡ይከማቻሉ፤
እንደ፡እሸትም፡ራስ፡ይቈረጣሉ።
25፤እንዲህስ፡ባይኾን፡ሐሰተኛ፡የሚያደርገኝ፥
ነገሬንስ፡እንደ፡ምናምን፡የሚያደርገው፡ማን፡ነው፧
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡25።______________
ምዕራፍ፡25።
1፤ሹሐዊውም፡በልዳዶስ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ገዢነትና፡መፈራት፡በርሱ፡ዘንድ፡ናቸው፤
በከፍታውም፡ሰላም፡አድራጊ፡ነው።
3፤በእውኑ፡ለሰራዊቶቹ፡ቍጥር፡አላቸውን፧
ብርሃኑስ፡የማይወጣው፡በማን፡ላይ፡ነው፧
4፤ሰውስ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ጻድቅ፡ይኾን፡ዘንድ፥
ከሴትስ፡የተወለደ፡ንጹሕ፡ይኾን፡ዘንድ፡እንዴት፡ይችላል፧
5፤እንሆ፥ጨረቃ፡እንኳ፡ብሩህ፡አይደለም፥
ከዋክብትም፡በፊቱ፡ንጹሓን፡አይደሉም።
6፤ይልቁንስ፡ብስብስ፡የኾነ፡ሰው፥
ትልም፡የኾነ፡የሰው፡ልጅ፡ምንኛ፡ያንስ!
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡26።______________
ምዕራፍ፡26።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ኀይል፡የሌለውን፡ምንኛ፡ረዳኸው!
ብርታት፡የሌለውን፡ክንድ፡ምንኛ፡አዳንኸው!
3፤ጥበብስ፡የሌለውን፡ምንኛ፡መከርኸው!
ብዙ፡ዕውቀትንስ፡ምንኛ፡ገለጥኽለት!
4፤ይህንስ፡ቃል፡በማን፡ርዳታ፡ተናገርኽ፧
የማንስ፡መንፈስ፡ከአንተ፡ዘንድ፡ወጣ፧
5፤ሙታን፡ሰዎች፡ከውሃዎች፡በታች፥
በውሃዎችም፡ውስጥ፡ከሚኖሩ፡በታች፡ይንቀጠቀጣሉ።
6፤ሲኦል፡በፊቱ፡ዕራቍቷን፡ናት፥
ለጥፋትም፡መጋረጃ፡የለውም።
7፤ሰሜንን፡በባዶ፡ስፍራ፡ላይ፡ይዘረጋል፥
ምድሪቱንም፡በታቿ፡አንዳች፡አልባ፡ያንጠለጥላል።
8፤ውሃዎችን፡በደመናዎቹ፡ውስጥ፡ያስራል፥
ደመናዪቱም፡ከታች፡አልተቀደደችም።
9፤የዙፋኑን፡ፊት፡ይከድናል፥
ደመናውንም፡ይዘረጋበታል።
10፤ብርሃንና፡ጨለማ፡እስከሚለያዩበት፡ዳርቻ፡ድረስ፥
በውሃዎች፡ፊት፡ላይ፡ድንበርን፡አደረገ።
11፤የሰማይ፡አዕማድ፡ይንቀጠቀጣሉ፥
ከተግሣጹም፡የተነሣ፡ይደነግጣሉ።
12፤በኀይሉ፡ባሕርን፡ጸጥ፡ያደርጋል፥
በማስተዋሉም፡ረዓብን፡ይመታል።
13፤በመንፈሱ፡ሰማያት፡ውበትን፡አገኙ፥
እጁም፡በራሪዪቱን፡እባብ፡ወጋች።
14፤እንሆ፥ይህ፡የመንገዱ፡ዳርቻ፡ብቻ፡ነው፤
ይህም፡የሰማነው፡ነገር፡ምንኛ፡ጥቂት፡ነው!
የኀይሉንስ፡ነጐድጓድ፡ያስተውል፡ዘንድ፡ማን፡ይችላል፧
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡27።______________
ምዕራፍ፡27።
1፤ኢዮብም፡ምሳሌውን፡ይመስል፡ዘንድ፡ደገመ፥እንዲህም፡አለ፦
2፤ፍርዴን፡ያስወገደ፡ሕያው፡እግዚአብሔርን!
ነፍሴንም፡መራራ፡ያደረገ፡ዅሉን፡የሚችል፡ሕያው፡አምላክን!
3፤እስትንፋሴ፡በእኔ፡ውስጥ፥
የእግዚአብሔርም፡መንፈስ፡ባፍንጫዬ፡ውስጥ፡ገና፡ሳለ፥
4፤ከንፈሬ፡ኀጢአትን፡አትናገርም፥
አንደበቴም፡ሽንገላን፡አያወጣም።
5፤እናንተን፡ማጽደቅ፡ከእኔ፡ዘንድ፡ይራቅ፤
እስክሞት፡ድረስ፡ፍጹምነቴን፡ከእኔ፡አላርቅም።
6፤ጽድቄን፡እይዛለኹ፡ርሱንም፡አልተውም፤
ከቀኖቼም፡ዅሉ፡ስለ፡አንዱ፡ልቤ፡አይዘልፈኝም።
7፤ጠላቴ፡እንደ፡በደለኛ፥
በእኔ፡ላይም፡የሚነሣ፡እንደ፡ኀጢአተኛ፡ይኹን።
8፤እግዚአብሔር፡ባጠፋውና፡ነፍሱን፡በለየ፡ጊዜ፥
የዝንጉ፡ሰው፡ተስፋው፡ምንድር፡ነው፧
9፤በእውኑ፡መከራ፡በመጣበት፡ጊዜ፥
እግዚአብሔር፡ጩኸቱን፡ይሰማልን፧
10፤ዅሉንስ፡በሚችል፡አምላክ፡ደስ፡ይለዋልን፧
እግዚአብሔርንስ፡ዅልጊዜ፡ይጠራልን፧
11፤እኔ፡ስለእግዚአብሔር፡እጅ፡አስተምራችዃለኹ፤
ዅሉን፡በሚችል፡አምላክ፡ዘንድ፡ያለውን፡አልሸሽግም።
12፤እንሆ፥ዅላችኹ፡አይታችዃል፤
ስለ፡ምን፡ከንቱ፡ኾናችኹ፧
13፤ይህች፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የበደለኛ፡ዕድል፡ፈንታ፥
ግፈኛም፡ዅሉን፡ከሚችል፡አምላክ፡ዘንድ፡የሚቀበላት፡ርስት፡ናት፤
14፤ልጆቹ፡ቢበዙ፡ለሰይፍ፡ይኾናሉ፤
ዘሩም፡እንጀራን፡አይጠግብም።
15፤ለርሱም፡የቀሩት፡በቸነፈር፡ይቀበራሉ፤
መበለቶቻቸውም፡አያለቅሱም።
16፤ርሱ፡ብርን፡እንደ፡ዐፈር፡ቢከምር፥
ልብስንም፡እንደ፡ጭቃ፡ቢያዘጋጅ፥
17፤ርሱ፡ያዘጋጀው፡ይኾናል፥ነገር፡ግን፥ጻድቅ፡ይለብሰዋል፤
ብሩንም፡ንጹሓን፡ይከፋፈሉታል።
18፤የሚሠራው፡ቤት፡እንደ፡ሸረሪት፡ድር፡ይሠራል፥
ጠባቂም፡እንደሚሠራው፡ጐዦ፡ነው።
19፤ባለጠጋ፡ኾኖ፡ይተኛል፥ዳግመኛም፡አይተኛም፤
ዐይኑን፡ይከፍታል፥ርሱም፡የለም።
20፤ድንጋጤ፡እንደ፡ጐርፍ፡ታገኘዋለች፤
በሌሊትም፡ዐውሎ፡ነፋስ፡ትነጥቀዋለች።
21፤የምሥራቅ፡ነፋስ፡ያነሣዋል፥ርሱም፡ይኼዳል፤
ከቦታውም፡ይጠርገዋል።
22፤ርሱ፡ይጥልበታል፥አይራራለትም፤
ከእጁ፡ፈጥኖ፡መሸሽ፡ይወዳ፟ል።
23፤ሰው፡በእጁ፡ያጨበጭብበታል፤
ከስፍራውም፡በፉጨት፡ያስወጡታል።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡28።______________
ምዕራፍ፡28።
1፤በእውነት፡ብር፡የሚወጣበት፥
ወርቅም፡የሚነጠርበት፡ስፍራ፡አለ።
2፤ብረት፡ከመሬት፡ውስጥ፡ይወሰዳል፤
መዳብም፡ከድንጋይ፡ይቀለጣል።
3፤ሰው፡ለጨለማ፡ፍጻሜን፡ያደርጋል፤
የጨለማውንና፡የሞት፡ጥላን፡ድንጋይ፡እስከ፡ወሰኑ፡ድረስ፡ይፈላልጋል።
4፤ሰው፡ከሚኖርበት፡ርቀው፡መውረጃ፡ይቈፍራሉ፤
ከሰውም፡እግር፡ተረሱ፥
ከሰዎችም፡ርቀው፡እየተንጠለጠሉ፡ይወዛወዛሉ።
5፤እንጀራ፡ከምድር፡ውስጥ፡ይወጣል፤
በእሳትም፡እንደሚኾን፡ታችኛው፡ይገለበጣል።
6፤ድንጋይዋ፡የሰንፔር፡ስፍራ፡ነው፥
የወርቅም፡ድቃቂ፡አለው።
7፤መንገዷን፡ጭልፊት፡አያውቀውም፥
የአሞራም፡ዐይን፡አላየውም።
8፤የትዕቢት፡ልጆች፡አልረገጧትም፥
ደቦል፡አንበሳ፡አላለፈባትም።
9፤ሰው፡ወደ፡ቡላድ፡ድንጋይ፡እጁን፡ይዘረጋል፥
ተራራውንም፡ከመሠረቱ፡ይገለብጣል።
10፤ከድንጋይ፡ውስጥ፡መንዶልዶያ፡ይወቅራል፤
ዐይኑም፡ዕንቍን፡ዅሉ፡ታያለች።
11፤ፈሳሹም፡እንዳይንጠባጠብ፡ይገድባል፤
የተሰወረውንም፡ነገር፡ወደ፡ብርሃን፡ያወጣል።
12፤ነገር፡ግን፥ጥበብ፡የምትገኘው፡ወዴት፡ነው፧
የማስተዋልስ፡ስፍራ፡ወዴት፡ነው፧
13፤ሰው፡መንገዷን፡አያውቅም፤
በሕያዋን፡ምድር፡አትገኝም።
14፤ቀላይ፦በእኔ፡ውስጥ፡የለችም፡ይላል፤
ባሕርም፦በእኔ፡ዘንድ፡የለችም፡ይላል።
15፤በምዝምዝ፡ወርቅ፡አትገኝም፥
ብርም፡ስለ፡ዋጋዋ፡አይመዘንም።
16፤በኦፊር፡ወርቅ፥
በከበረም፡መረግድና፡በሰንፔር፡አትገመትም።
17፤ወርቅና፡ብርጭቆ፡አይወዳደሯትም፥
በጥሩ፡ወርቅም፡ዕቃ፡አትለወጥም።
18፤ስለ፡ዛጐልና፡ስለ፡አልማዝ፡አይነገርም።
የጥበብ፡ዋጋ፡ከቀይ፡ዕንቍ፡ይልቅ፡ይበልጣል።
19፤የኢትዮጵያ፡ቶጳዝዮን፡አይተካከላትም፥
በጥሩም፡ወርቅ፡አትገመትም።
20፤እንግዲያሳ፡ጥበብ፡ከወዴት፡ትመጣለች፧
የማስተዋልስ፡ስፍራ፡ወዴት፡ነው፧
21፤ከሕያዋን፡ዅሉ፡ዐይን፡ተሰውራለች፥
ከሰማይ፡ወፎች፡ተሸሽጋለች።
22፤ጥፋትና፡ሞት፦ወሬዋን፡በዦሮዎቻችን፡ሰማን፡ብለዋል።
23፤እግዚአብሔር፡መንገዷን፡ያስተውላል፥
ርሱም፡ስፍራዋን፡ያውቃል።
24፤ርሱም፡የምድርን፡ዳርቻ፡ይመለከታል፥
ከሰማይም፡በታች፡ያለውን፡ዅሉ፡ያያል።
25፤ለነፋስ፡ሚዛንን፡ባደረገለት፡ጊዜ፥
ውሃዎችንም፡በስፍር፡በሰፈረ፡ጊዜ፥
26፤ለዝናብም፡ሥርዐትን፥
ለነጐድጓድ፡መብረቅም፡መንገድን፡ባደረገ፡ጊዜ፥
27፤በዚያን፡ጊዜ፡አያት፥ገለጣትም፤
አዘጋጃትም፥ደግሞም፡መረመራት።
28፤ሰውንም፦እንሆ፥እግዚአብሔርን፡መፍራት፡ጥበብ፡ነው፤
ከኀጢአትም፡መራቅ፡ማስተዋል፡ነው፡አለው።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡29።______________
ምዕራፍ፡29።
1፤ኢዮብም፡ምሳሌውን፡ይመስል፡ዘንድ፡ደገመ፥እንዲህም፡አለ፦
2፤እግዚአብሔር፡ይጠብቀኝ፡እንደ፡ነበረው፡ጊዜ፥
እንደ፡ፊተኛው፡ወራት፡ምነው፡በኾንኹ!
3፤በራሴ፡ላይ፡መብራቱ፡በበራ፡ጊዜ፥
እኔም፡ጨለማውን፡ዐልፌ፡በብርሃኑ፡በኼድኹ፡ጊዜ፥
4፤በሙሉ፡ሰውነቴ፡እንደ፡ነበርኹ፡ጊዜ፥
እግዚአብሔር፡ድንኳኔን፡በጋረደ፡ጊዜ፥
5፤ዅሉን፡የሚችል፡አምላክ፡ከእኔ፡ጋራ፡ገና፡ሳለ፥
ልጆቼም፡በዙሪያዬ፡ሳሉ፥
6፤መንገዴ፡በቅቤ፡ይታጠብ፡በነበረ፡ጊዜ፥
ድንጋዩ፡የዘይት፡ፈሳሽ፡ያፈስ፟ልኝ፡በነበረ፡ጊዜ።
7፤ወደከተማዪቱ፡በር፡በወጣኹ፡ጊዜ፥
በአደባባዩም፡ወንበሬን፡ባኖርኹ፡ጊዜ፥
8፤ጐበዛዝት፡እኔን፡አይተው፡ተሸሸጉ፥
ሽማግሌዎችም፡ተነሥተው፡ቆሙ።
9፤አለቃዎቹ፡ከመናገር፡ዝም፡አሉ፥
እጃቸውንም፡በአፋቸው፡ላይ፡ጫኑ።
10፤የታላላቆቹም፡ድምፅ፡አረመመ፤
ምላሳቸውም፡በትናጋቸው፡ተጣጋ።
11፤የሰማችኝ፡ዦሮ፡አሞገሰችኝ፥
ያየችኝም፡ዐይን፡መሰከረችልኝ፤
12፤የሚጮኸውን፡ችግረኛ፥
ድኻ፡አደጉንና፡ረጂ፡የሌለውን፡አድኜ፡ነበርና።
13፤ለጥፋት፡የቀረበው፡በረከት፡በላዬ፡መጣ፤
የባልቴቲቱንም፡ልብ፡እልል፡አሠኘኹ።
14፤ጽድቅን፡ለበስኹ፡ርሷም፡ለበሰችኝ፤
ፍርዴም፡እንደ፡መጐናጸፊያና፡እንደ፡ኵፋር፡ነበረ።
15፤ለዕውር፡ዐይን፥
ለዐንካሳ፡እግር፡ነበርኹ።
16፤ለድኻው፡አባት፡ነበርኹ፤
የማላውቀውንም፡ሰው፡ሙግት፡መረመርኹ።
17፤የኀጢአተኛውን፡መንጋጋ፡ሰበርኹ፥
የነጠቀውንም፡ከጥርሱ፡ውስጥ፡አስጣልኹ።
18፤እኔም፡አልኹ፦በልጆቼ፡መካከል፡እሞታለኹ፥
ዕድሜዬንም፡እንደ፡አሸዋ፡አበዛለኹ፤
19፤ሥሬ፡በውሃ፡ላይ፡ተዘርግቷል፥
ጠልም፡በቅርንጫፌ፡ላይ፡ያድራል፤
20፤ክብሬ፡በእኔ፡ዘንድ፡ታድሷል፥
ቀስቴም፡በእጄ፡ውስጥ፡ለምልሟል።
21፤ሰዎች፡እኔን፡ሰምተው፡በትዕግሥት፡ተጠባበቁ፥
ምክሬንም፡ለማዳመጥ፡ዝም፡አሉ።
22፤ከቃሌ፡በዃላ፡አንዳች፡አልመለሱም፤
ንግግሬም፡በርሱ፡ላይ፡ተንጠባጠበ።
23፤ዝናብን፡እንደሚጠብቁ፡በትዕግሥት፡ጠበቁኝ፤
የጥቢን፡ዝናብ፡እንደሚሹ፡አፋቸውን፡ከፈቱ።
24፤እነርሱ፡ባልታመኑ፡ጊዜ፡ሣቅኹላቸው፤
የፊቴንም፡ብርሃን፡አላወረዱም።
25፤መንገዳቸውን፡መረጥኹ፤
እንደ፡አለቃ፡ኾኜ፡ተቀመጥኹ፤
ንጉሥ፡በሰራዊቱ፡መካከል፡እንደሚኖር፥
ሐዘነተኛዎችን፡እንደሚያጽናና፡ኖርኹ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡30።______________
ምዕራፍ፡30።
1፤አኹን፡ግን፡በዕድሜ፡ከእኔ፡የሚያንሱ፥
አባቶቻቸውን፡ከመንጋዬ፡ውሻዎች፡ጋራ፡ለማኖር፡የናቅዃቸው፥
በእኔ፡ላይ፡ተሣለቁብኝ።
2፤ሙሉ፡ሰው፡መኾናቸው፡ጠፍቶባቸው፡ነበርና፥
የእጃቸው፡ብርታት፡ለእኔ፡ምን፡ይጠቅማል፧
3፤በራብና፡በቀጠና፡የመነመኑ፡ናቸው፤
የመፍረስና፡የመፈታት፡ጨለማ፡ወዳለበት፡
ወደ፡ምድረ፡በዳ፡ይሸሻሉ።
4፤በቍጥቋጦ፡አጠገብ፡ያለውን፡
ጨው፡ጨው፡የሚለውን፡አትክልት፡ይለቅማሉ፤
የክትክታ፡ሥር፡ደግሞ፡መብላቸው፡ነው።
5፤ከሰዎች፡ተለይተው፡ተሰደዱ፤
በሌባ፡ላይ፡እንደሚጮኽ፡ይጮኹባቸዋል።
6፤በሸለቆ፡ፈረፈርና፡በምድር፡ጕድጓድ፡
በድንጋይም፡ዋሻ፡ውስጥ፡ይኖራሉ።
7፤በቍጥቋጦ፡መካከል፡ይጮኻሉ፤
ከሳማ፡በታች፡ተሰብስበዋል።
8፤የሰነፎችና፡የነውረኛዎች፡ልጆች፡ናቸው፤
ከምድርም፡በግርፋት፡የተባረሩ፡ናቸው።
9፤አኹንም፡እኔ፡መዝፈኛና፡መተረቻ፡ኾንዃቸው።
10፤ተጸየፉኝ፥ከእኔም፡ራቁ፤
አክታቸውንም፡በፊቴ፡መትፋትን፡አልተዉም።
11፤የቀስቴን፡አውታር፡አላልቶብኛል፥አዋርዶኝማል፤
እነርሱም፡በፊቴ፡ልጓማቸውን፡ፈተ፟ዋል።
12፤በቀኜ፡በኩል፡ዱርዬዎች፡ተነሥተዋል፥
እግሬንም፡ይገለብጣሉ፤
የጥፋታቸውን፡መንገድ፡በእኔ፡ላይ፡ይጐድባሉ።
13፤ጐዳናዬን፡ያበላሻሉ፤
ረዳት፡የሌላቸው፡ሰዎች፡መከራዬን፡ያበዛሉ።
14፤በሰፊ፡ፍራሽ፡እንደሚመጡ፡ይመጡብኛል፤
በባድማ፡ውስጥ፡ይንከባለሉብኛል።
15፤ድንጋጤ፡በላዬ፡ተመለሰችብኝ፥
ክብሬንም፡እንደ፡ነፋስ፡ያሳድዷታል፤
ደኅንነቴም፡እንደ፡ደመና፡ዐልፋለች።
16፤አኹንም፡ነፍሴ፡በውስጤ፡ፈሰሰች፤
የመከራም፡ዘመን፡ያዘችኝ።
17፤በሌሊት፡ዐጥንቴ፡በደዌ፡ተነደለች፥
ዥማቶቼም፡አያርፉም።
18፤ከታላቁ፡ደዌ፡ኀይል፡የተነሣ፡ልብሴ፡ተበላሸች፤
እንደ፡ቀሚስ፡ክሳድ፡ዐነቀችኝ።
19፤ርሱ፡በጭቃ፡ውስጥ፡ጣለኝ፥
ዐፈርና፡ዐመድም፡መሰልኹ።
20፤ወዳንተ፡ጮኽኹ፥አልመለስኽልኝም፤
ተነሣኹ፥አልተመለከትኸኝም።
21፤ተመልሰኽ፡ጨካኝ፡ኾንኽብኝ፤
በእጅኽም፡ብረታት፡አስጨነቅኸኝ።
22፤በነፋስ፡አነሣኸኝ፥በላዩም፡አስቀመጥኸኝ፤
በዐውሎ፡ነፋስ፡አቀለጥኸኝ።
23፤ለሞት፡ሕያዋንም፡ዅሉ፡ለሚሰበሰቡበት፡ቤት፡አሳልፈኽ፡እንደምትሰጠኝ፡ዐውቄያለኹና።
24፤ነገር፡ግን፥ሰው፡በወደቀ፡ጊዜ፡እጁን፡አይዘረጋምን፧
በጥፋቱስ፡ጊዜ፡አይጮኽምን፧
25፤ጭንቅ፡ቀን፡ላገኘው፡ሰው፡አላለቀስኹምን፧
ለችግረኛስ፡ነፍሴ፡አላዘነችምን፧
26፤ነገር፡ግን፥በጎነትን፡በተጠባበቅኹ፡ጊዜ፡ክፉ፡ነገር፡መጣችብኝ፤
ብርሃንን፡በትዕግሥት፡ጠበቅኹ፥ጨለማም፡መጣ።
27፤አንዠቴ፡ፈላች፥አላረፈችም፤
የመከራም፡ዘመን፡መጣችብኝ።
28፤ያለፀሓይ፡በትካዜ፡ኼድኹ፤
በጉባኤም፡መካከል፡ቆሜ፡ጮኽኹ።
29፤ለቀበሮ፡ወንድም፥
ለሰጐንም፡ባልንጀራ፡ኾንኹ።
30፤ቍርበቴ፡ጠቈረ፥ከእኔም፡ተለይቶ፡ርግፍግፍ፡አለ፤
ዐጥንቴም፡ከትኵሳት፡የተነሣ፡ተቃጠለች።
31፤ስለዚህ፥መሰንቆዬ፡ለሐዘን፥
እንቢልታዬም፡ለሚያለቅሱ፡ቃል፡ኾነ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡31።______________
ምዕራፍ፡31።
1፤ከዐይኔ፡ጋራ፡ቃል፡ኪዳን፡ገባኹ፤
እንግዲህስ፡ቈንዦዪቱን፡እንዴት፡እመለከታለኹ፧
2፤የእግዚአብሔር፡ዕድል፡ፈንታ፡ከላይ፥
ዅሉንም፡የሚችል፡አምላክ፡ርስት፡ከአርያም፡ምንድር፡ነው፧
3፤መዓትስ፡ለኀጢአተኛ፥
መለየትስ፡ለሚበድሉ፡አይደለችምን፧
4፤መንገዴን፡አያይምን፧
ርምጃዬንስ፡ዅሉ፡አይቈጥርምን፧
5፤6፤በእውነተኛ፡ሚዛን፡ልመዘን፥
እግዚአብሔርም፡ቅንነቴን፡ይወቅ።
በሐሰት፡ኼጄ፡እንደ፡ኾነ፡
እግሬም፡ለሽንገላ፡ቸኵላ፡እንደ፡ኾነ፥
7፤ርምጃዬ፡ከመንገድ፡ፈቀቅ፡ብሎ፥
ልቤም፡ዐይኔን፡ተከትሎ፥
ነውርም፡ከእጄ፡ጋራ፡ተጣብቆ፡እንደ፡ኾነ፥
8፤እኔ፡ልዝራ፥ሌላ፡ሰውም፡ይብላው፤
የሚበቅለውም፡ዅሉ፡ይነቀል።
9፤ልቤ፡ወደ፡ሌላዪቱ፡ሴት፡ጐምዥቶ፡እንደ፡ኾነ፥
በባልንጀራዬም፡ደጅ፡አድብቼ፡እንደ፡ኾነ፥
10፤ሚስቴ፡ለሌላ፡ሰው፡ትፍጭ፥
ሌላዎችም፡በርሷ፡ላይ፡ይጐንበሱ።
11፤ይህ፡ክፉ፡አበሳ፥
ፈራጆችም፡የሚቀጡበት፡በደል፡ነውና፤
12፤ይህ፡እስከ፡ጥፋት፡ድረስ፡የሚበላ፡እሳት፥
ቡቃያዬንም፡ዅሉ፡የሚነቅል፡ነውና።
13፤ወንድ፡ባሪያዬ፡ወይም፡ሴት፡ባሪያዬ፡ከእኔ፡ጋራ፡በተሟገቱ፡ጊዜ፥
ሙግታቸውን፡ንቄ፡እንደ፡ኾነ፥
14፤እግዚአብሔር፡በተነሣ፡ጊዜ፡ምን፡አደርጋለኹ፧
በጐበኘኝ፡ጊዜ፡ምን፡እመልስለታለኹ፧
15፤እኔን፡በማሕፀን፡የፈጠረ፡ርሱንስ፡የፈጠረው፡አይደለምን፧
በማሕፀንስ፡ውስጥ፡የሠራን፡አንድ፡አይደለንምን፧
16፤ድኻውን፡ከልመናው፡ከልክዬ፥
የመበለቲቱን፡ዐይን፡አጨልሜ፡እንደ፡ኾነ፥
17፤እንጀራዬን፡ለብቻዬ፡በልቼ፡እንደ፡ኾነ፥
ድኻ፡አደጉም፡ደግሞ፡ከርሱ፡ሳይበላ፡ቀርቶ፡እንደ፡ኾነ፤
18፤ርሱን፡ግን፡ከታናሽነቴ፡ዠምሬ፡እንደ፡አባቱ፡ከእኔ፡ጋራ፡አሳድጌው፡ነበር፥
ርሷንም፡ከእናቴ፡ማሕፀን፡ዠምሬ፡መራዃት፤
19፤ዕራቍቱን፡የኾነው፡ሰው፡ሲጠፋ፥
ወይም፡ድኻ፡ያለልብስ፡ሲኾን፡አይቼ፡እንደ፡ኾነ፥
20፤ጐንና፡ጐኑ፡ያልባረከችኝ፥
በበጎቼም፡ጠጕር፡ያልሞቀ፡እንደ፡ኾነ፤
21፤በበሩ፡ረዳት፡ስላየኹ፥
በድኻ፡አደጉ፡ላይ፡እጄን፡አንሥቼ፡እንደ፡ኾነ፥
22፤ትከሻዬ፡ከመሠረቷ፡ትውደቅ፥
ክንዴም፡ከመገናኛዋ፡ትሰበር።
23፤የእግዚአብሔር፡መዓት፡አስደንግጦኛልና፤
በክብሩም፡ፊት፡ምንም፡ለማድረግ፡አልቻልኹም።
24፤ወርቅን፡ተስፋ፡አድርጌ፥
ጥሩውንም፡ወርቅ፦ባንተ፡እታመናለኹ፡ብዬ፡እንደ፡ኾነ፤
25፤ሀብቴ፡ስለ፡በዛ፥
እጄም፡ብዙ፡ስላገኘች፡ደስ፡ብሎኝ፡እንደ፡ኾነ፤
26፤ፀሓይ፡ሲበራ፡
ጨረቃ፡በክብር፡ስትኼድ፡አይቼ፥
27፤ልቤ፡በስውር፡ተታሎ፟፥
አፌም፡እጄን፡ስሞ፡እንደ፡ኾነ፤
28፤ልዑል፡እግዚአብሔርን፡በካድኹ፡ነበርና፥
ይህ፡ደግሞ፡ፈራጆች፡የሚቀጡበት፡በደል፡በኾነ፡ነበር።
29፤በሚጠላኝ፡መጥፋት፡ደስ፡ብሎኝ፡
ክፉ፡ነገርም፡ባገኘው፡ጊዜ፡ሐሤት፡አድርጌ፡እንደ፡ኾነ፤
30፤ነገር፡ግን፥በመርገም፡ነፍሱን፡በመሻት፡
አንደበቴን፡ኀጢአት፡ይሠራ፡ዘንድ፡አልሰጠኹም፤
31፤በድንኳኔ፡የሚኖሩ፡ሰዎች፦
በከብቱ፡ሥጋ፡ያልጠገበ፡ማን፡ይገኛል፧ብለው፡እንደ፡ኾነ፤
32፤መጻተኛው፡ግን፡በሜዳ፡አያድርም፡ነበር፥
ደጄንም፡ለመንገደኛ፡እከፍት፡ነበር፤
33፤በደሌንም፡በብብቴ፡በመሸሸግ፡
ኀጢአቴን፡እንደ፡ሰው፡ሰውሬ፡እንደ፡ኾነ፤
34፤ከሕዝብ፡ብዛት፡ፈርቼ፥
የዘመዶቼም፡ንቀት፡አስደንግጦኝ፥
ዝም፡ብዬ፡ከደጅ፡ያልወጣኹ፡እንደ፡ኾነ፤
35፤የሚያዳምጠኝ፡ምነው፡በኖረልኝ!
እንሆ፥የእጄ፡ምልክት፡
ዅሉን፡የሚችል፡አምላክ፡ይመልስልኝ፤
ከባላጋራዬ፡የተጻፈው፡የክስ፡ጽሑፍ፡ምነው፡በተገኘልኝ!
36፤በትከሻዬ፡ላይ፡እሸከመው፥
አክሊልም፡አድርጌ፡በራሴ፡አስረው፡ነበር፤
37፤የርምጃዬን፡ቍጥር፡አስታውቀው፥
እንደ፡አለቃም፡ኾኜ፡አቀርብለት፡ነበር።
38፤ዕርሻዬ፡በእኔ፡ላይ፡ጮኻ፡እንደ፡ኾነ፥
ትልሞቿም፡ባንድ፡ላይ፡አልቅሰው፡እንደ፡ኾነ፤
39፤ፍሬዋን፡ያለዋጋ፡በልቼ፥
የባለቤቶችንም፡ነፍስ፡አሳዝኜ፡እንደ፡ኾነ፥
40፤በስንዴ፡ፋንታ፡አሜከላ፥
በገብስም፡ፋንታ፡ኵርንችት፡ይውጣብኝ።የኢዮብ፡ቃል፡ተፈጸመ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡32።______________
ምዕራፍ፡32።
1፤ኢዮብም፡ራሱን፡ጻድቅ፡አድርጎ፡ነበርና፥እነዚያ፡ሦስቱ፡ሰዎች፡መመለስን፡ተዉ።
2፤ከራም፡ወገን፡የኾነ፡የቡዛዊው፡የባርክኤል፡ልጅ፡የኤሊሁ፡ቍጣ፡ነደደ፤ከእግዚአብሔር፡ይልቅ፡ራሱን፡ጻድቅ ፡አድርጎ፡ነበርና፥ኢዮብን፡ተቈጣው።
3፤ደግሞም፡በኢዮብ፡ፈረዱበት፡እንጂ፡የሚገ፟ባ፟፡መልስ፡ስላላገኙ፥በሦስቱ፡ባልንጀራዎቹ፡ላይ፡ተቈጣ።
4፤ኤሊሁ፡ግን፡ከርሱ፡ይልቅ፡ሽማግሌዎች፡ነበሩና፥ከኢዮብ፡ጋራ፡መናገርን፡ጠብቆ፡ነበር።
5፤ኤሊሁም፡በነዚህ፡በሦስቱ፡ሰዎች፡አፍ፡መልስ፡እንደሌለ፡ባየ፡ጊዜ፡ቍጣው፡ነደደ።
6፤የቡዛዊውም፡የባርክኤል፡ልጅ፡ኤሊሁ፡ተናገረ፡እንዲህም፡አለ፦
እኔ፡በዕድሜ፡ታናሽ፡ነኝ፥እናንተ፡ግን፡ሽማግሌዎች፡ናችኹ፤
ስለዚህም፡ሠጋኹ፤ዕውቀቴን፡እገልጥላችኹ፡ዘንድ፡ፈራኹ።
7፤እንደዚህም፡አልኹ፦ዓመታት፡በተናገሩ፡ነበር፥
የዓመታትም፡ብዛት፡ጥበብን፡ባስተማረች፡ነበር።
8፤ነገር፡ግን፥በሰው፡ውስጥ፡መንፈስ፡አለ፥
ዅሉንም፡የሚችል፡የአምላክ፡እስትንፋስ፡ማስተዋልን፡ይሰጣል።
9፤በዕድሜ፡ያረጁ፡ጠቢባን፡አይደሉም፥
ሽማግሌዎችም፡ፍርድን፡አያስተውሉም።
10፤ስለዚህም፦ስሙኝ፤
እኔ፡ደግሞ፡ዕውቀቴን፡እገልጥላችዃለኹ፡አልኹ።
11፤እንሆ፥ቃላችኹን፡በትዕግሥት፡ጠበቅኹ፤
የምትናገሩትን፡ነገር፡እስክትመረምሩ፡ድረስ፤
ብልኀታችኹን፡አዳመጥኹ።
12፤እንዲሁም፡ልብ፡አደረግኹ፤
እንሆም፥በእናንተ፡መካከል፡ኢዮብን፡ያስረዳ፥
ወይም፡ለቃሉ፡የመለሰ፡የለም።
13፤እናንተም፦ጥበብን፡አግኝተናል፤
እግዚአብሔር፡ነው፡እንጂ፡ሰው፡አያሸንፈውም፡እንዳትሉ፡ተጠንቀቁ።
14፤ርሱ፡ግን፡ቃሉን፡በእኔ፡ላይ፡አልተናገረም፤
እኔም፡በንግግራችኹ፡አልመልስለትም።
15፤እነርሱ፡ደነገጡ፥ዳግመኛም፡አልመለሱም፤
የሚናገሩትንም፡ዐጡ።
16፤እነርሱ፡አልተናገሩምና፥
ቆመው፡ዳግመኛ፡አልመለሱምና፡እኔ፡በትዕግሥት፡እጠብቃለኹን፧
17፤እኔ፡ደግሞ፡ፈንታዬን፡እመልሳለኹ፥
ዕውቀቴንም፡እገልጣለኹ፤
18፤እኔ፡ቃል፡ተሞልቻለኹና፥
በውስጤም፡ያለ፡መንፈስ፡አስገድዶኛልና።
19፤በተሓ፡ጠጅ፡እንደ፡ተሞላና፡ሊቀደድ፡እንደ፡ቀረበ፡አቍማዳ፥
ሊፈነዳ፡እንደማይችል፡እንደ፡ወይን፡ጠጅ፡
አቍማዳ፥እንሆ፥አንዠቴ፡ኾነ።
20፤ጥቂት፡እንድተነፍስ፡እናገራለኹ፤
ከንፈሬን፡ገልጬ፡እመልሳለኹ።
21፤ለሰው፡ፊት፡ግን፡አላደላም፤
ሰውንም፡አላቈላምጥም።
22፤በማቈላመጥ፡እናገር፡ዘንድ፡አላውቅምና፤
ያለዚያስ፡ፈጣሪዬ፡ፈጥኖ፡ከሕይወቴ፡ይለየኝ፡ነበር።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡33።______________
ምዕራፍ፡33።
1፤ነገር፡ግን፥ኢዮብ፡ሆይ፥ንግግሬን፡እንድትሰማ፥
ቃሌንም፡ዅሉ፡እንድታደምጥ፡እለምንኻለኹ።
2፤እንሆ፥አፌን፡ከፍቻለኹ፥
አንደበቴም፡በትናጋዬ፡ተናግሯል።
3፤ቃሌ፡የልቤን፡ቅንነት፡ያወጣል፤
ከንፈሮቼም፡የሚያውቁትን፡በቅንነት፡ይናገራሉ።
4፤የእግዚአብሔር፡መንፈስ፡ፈጠረኝ፥
ዅሉንም፡የሚችል፡የአምላክ፡እስትንፋስ፡ሕይወት፡ሰጠኝ።
5፤ይቻልኽ፡እንደ፡ኾነ፡መልስልኝ፤
ቃልኽንም፡አዘጋጅተኽ፡በፊቴ፡ቁም።
6፤እንሆ፥በእግዚአብሔር፡ፊት፡እኔ፡እንደ፡አንተ፡ነኝ፤
እኔ፡ደግሞ፡ከጭቃ፡የተፈጠርኹ፡ነኝ።
7፤እንሆ፥ግርማዬ፡አታስፈራኽም፡
እጄም፡አትከብድብኽም።
8፤በዦሮዬ፡ተናግረኻል፥
የቃልኽንም፡ድምፅ፡ሰምቻለኹ፥እንዲህም፡ብለኻል።
9፤እኔ፡ያለመተላለፍ፡ንጹሕ፡ነኝ፤
ያለነውር፡ነኝ፥ኀጢአትም፡የለብኝም፤
10፤እንሆ፥ምክንያት፡አግኝቶብኛል፥
እንደ፡ጠላቱም፡ቈጥሮኛል፤
11፤እግሬን፡በግንድ፡አጣበቀ፥
መንገዴንም፡ዅሉ፡ተመለከተ።
12፤እንሆ፥አንተ፡በዚህ፡ጻድቅ፡አይደለኽም፤
እግዚአብሔር፡ከሰው፡ይበልጣል፡ብዬ፡እመልስልኻለኹ።
13፤አንተ፦ለቃሌ፡ዅሉ፡አይመልስልኝም፡ብለኽ፥
ስለ፡ምን፡ከርሱ፡ጋራ፡ትከራከራለኽ፧
14፤እግዚአብሔር፡ባንድ፡መንገድ፡በሌላም፡ይናገራል፤
ሰው፡ግን፡አያስተውለውም።
15፤በሕልም፥በሌሊት፡ራእይ፥
ዐፍላ፡እንቅልፍ፡በሰዎች፡ላይ፡ሲወድቅ፥
በዐልጋ፡ላይ፡ተኝተው፡ሳሉ፥
16፤በዚያን፡ጊዜ፡የሰዎችን፡ዦሮ፡ይከፍታል፥
በተግሣጹም፡ያስደነግጣቸዋል፥
17፤ሰውን፡ከክፉ፡ሥራው፡ይመልሰው፡ዘንድ፡
ከሰውም፡ትዕቢትን፡ይሰውር፡ዘንድ፤
18፤ነፍሱን፡ከጕድጓድ፥
በሰይፍም፡እንዳይጠፋ፡ሕይወቱን፡ይጠብቃል።
19፤ደግሞ፡በዐልጋ፡ላይ፡በደዌ፡ይገሥጸዋል፥
ዐጥንቱንም፡ዅሉ፡ያደነዝዛል።
20፤ሕይወቱም፡እንጀራን፥
ነፍሱም፡ጣፋጭ፡መብልን፡ትጠላለች።
21፤ሥጋው፡እስከማይታይ፡ድረስ፡ይሰለስላል፤
ተሸፍኖ፡የነበረውም፡ዐጥንት፡ይገለጣል።
22፤ነፍሱ፡ወደ፡ጕድጓዱ፥
ሕይወቱም፡ወደሚገድሏት፡ቀርባለች።
23፤የቀናውን፡መንገድ፡ለሰው፡ያስታውቀው፡ዘንድ፥
ከሺሕ፡አንድ፡ኾኖ፡የሚተረጕም፡መልአክ፡ቢገኝለት፥
24፤እየራራለት።
ቤዛ፡አግኝቻለኹና፡
ወደ፡ጕድጓድ፡እንዳይወርድ፡አድነው፡ቢለው፥
25፤ሥጋው፡እንደ፡ሕፃን፡ሥጋ፡ይለመልማል፤
ወደጕብዝናውም፡ዘመን፡ይመለሳል።
26፤ወደ፡እግዚአብሔር፡ይጸልያል፥
ርሱም፡ሞገስን፡ይሰጠዋል፡
ፊቱንም፡በደስታ፡ያሳየዋል፤
ለሰውም፡ጽድቁን፡ይመልስለታል።
27፤ርሱም፡በሰው፡ፊት፡እየዘመረ፦
እኔ፡በድያለኹ፥ቅኑንም፡አጣምሜያለኹ፤
የሚገ፟ባ፟ኝንም፡ብድራት፡አልተቀበልኹም፤
28፤ነፍሴ፡ወደ፡ጕድጓድ፡እንዳትወርድ፡አድኗታል፥
ሕይወቴም፡ብርሃንን፡ታያለች፡ይላል።
29፤እግዚአብሔር፡ይህን፡ዅሉ፡
ኹለት፡ጊዜና፡ሦስት፡ጊዜ፡ከሰው፡ጋራ፡ያደርጋል፤
30፤ይህም፡ነፍሱን፡ከጕድጓድ፡ይመልስ፡ዘንድ፥
በሕያዋንም፡ብርሃን፡ያበራ፡ዘንድ፡ነው።
31፤ኢዮብ፡ሆይ፥አድምጥ፥እኔንም፡ስማ፤
ዝም፡በል፥እኔም፡እናገራለኹ።
32፤ነገር፡ቢኖርኽ፡መልስልኝ፤
ትጸድቅ፡ዘንድ፡እወዳ፟ለኹና፡ተናገር።
33፤ያለዚያም፡እኔን፡ስማ፤
ዝም፡በል፥እኔም፡ጥበብን፡አስተምርኻለኹ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡34።______________
ምዕራፍ፡34።
1፤ኤሊሁም፡ደግሞ፡መለሰ፥እንዲህም፡አለ፦
2፤እናንተ፡ጥበበኛዎች፥ቃሌን፡ስሙ፤
እናንተም፡ዐዋቂዎች፥ወደ፡እኔ፡አድምጡ።
3፤ትናጋ፡መብልን፡እንደሚቀምስ፥
ዦሮ፡ቃልን፡ትለያለችና።
4፤ቅን፡የኾነውን፡ነገር፡እንምረጥ፤
መልካሙንም፡ነገር፡በመካከላችን፡እንወቅ።
5፤ኢዮብ፦እኔ፡ጻድቅ፡ነኝ፥
እግዚአብሔር፡ግን፡ፍርዴን፡አስወገደ፤
6፤ምንም፡እውነተኛ፡ብኾን፡እንደ፡ውሸተኛ፡ተቈጠርኹ፤
ምንም፡ባልበድል፡ቍስሌ፡የማይፈወስ፡ነው፡ብሏል።
7፤8፤9፤ኢዮብም፦በእግዚአብሔር፡መደሰት፡
ለሰው፡ምንም፡አይጠቅምም፡ብሏልና፥
ከበደለኛዎች፡ጋራ፡የሚተባበር፥
ክፉ፡ከሚያደርጉስ፡ጋራ፡የሚኼድ፥
መሳለቅን፡እንደ፡ውሃ፡የሚጠጣት፡
እንደ፡ኢዮብ፡ያለ፡ሰው፡ማን፡ነው፧
10፤ስለዚህ፥እናንተ፡አእምሮ፡ያላችኹ፡ሰዎች፥ስሙኝ፤
ክፋትን፡ያደርግ፡ዘንድ፡ከእግዚአብሔር፥
በደልንም፡ይሠራ፡ዘንድ፡ዅሉን፡ከሚችል፡አምላክ፡ይራቅ።
11፤ለሰው፡ሥራውን፡ይመልስለታል፥
ሰውም፡እንደ፡መንገዱ፡ያገኝ፡ዘንድ፡ያደርጋል።
12፤በእውነት፡እግዚአብሔር፡ክፉ፡አይሠራም፥
ዅሉንም፡የሚችል፡አምላክ፡ፍርድን፡ጠማማ፡አያደርግም።
13፤ምድርን፡ዐደራ፡የሰጠው፡ማን፡ነው፧
ዓለምንስ፡ዅሉ፡በርሱ፡ላይ፡ያኖረ፡ማን፡ነው፧
14፤ርሱ፡ልቡን፡ወደ፡ራሱ፡ቢመልስ፥
መንፈሱንና፡እስትንፋሱን፡ወደ፡ራሱ፡ቢሰበስብ፥
15፤ሥጋ፡ለባሽ፡ዅሉ፡በአንድነት፡ይጠፋል፥
ሰውም፡ወደ፡ዐፈር፡ይመለሳል።
16፤አስተዋይ፡ብትኾን፡ይህን፡ስማ፤
የንግግሬንም፡ቃል፡አድምጥ።
17፤በእውኑ፡ጽድቅን፡የሚጠላ፡ይሠለጥናልን፧
ጻድቅና፡ኀያል፡የኾነውስ፡በደለኛ፡ታደርገዋለኽን፧
18፤ማንም፡ሰው፡ንጉሡን፦በደለኛ፡ነኽ፥
መኳንንቱንም፦ክፉዎች፡ናችኹ፡ይላልን፧
19፤እነርሱ፡ዅሉ፡የእጁ፡ሥራ፡ናቸውና፥
በአለቃዎች፡ፊት፡አያደላም፥
ባለጠጋውንም፡ሰው፡ከድኻው፡ይበልጥ፡አይመለከትም።
20፤እነርሱ፡በመንፈቀ፡ሌሊት፡በድንገት፡ይሞታሉ፤
ሕዝቡ፡ተንቀጥቅጦ፡ያልፋል፥
ኀያላንም፡ያለእጅ፡ይነጠቃሉ።
21፤ዐይኖቹ፡በሰው፡መንገድ፡ላይ፡ናቸው፥
ርምጃውንም፡ዅሉ፡ያያል።
22፤ኀጢአትን፡የሚሠሩ፡ይሰወሩበት፡ዘንድ፡
ጨለማ፡ወይም፡የሞት፡ጥላ፡የለም።
23፤ሰው፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለመፈራረድ፡እንዲመጣ፡
ጊዜ፡አይወሰንለትም።
24፤ታላላቆችን፡ያለምርመራ፡ይሰባብራል፥
በእነርሱም፡ፋንታ፡ሌላዎችን፡ያቆማል።
25፤ሥራቸውን፡ያውቃል፤
እንዲደቁ፟ም፡በሌሊት፡ይገለባብጣቸዋል።
26፤ሰዎች፡እያዩ፡እንደ፡ክፉዎች፡ይመታቸዋል፤
27፤28፤የድኻውን፡ልቅሶ፡ወደ፡ርሱ፡ያደርሱ፡ዘንድ፥
ርሱም፡የችግረኛውን፡ድምፅ፡ይሰማ፡ዘንድ፥
ርሱን፡ከመከተል፡ፈቀቅ፡ብለዋልና፥
ከመንገዱም፡ዅሉ፡አንዱን፡አልተመለከቱምና።
29፤በሕዝብ፡ወይም፡በሰው፡ዘንድ፡ቢኾን፥
ርሱ፡ቢያሳርፍ፡የሚፈርድ፡ማን፡ነው፧
ፊቱንስ፡ቢሰውር፡የሚያየው፡ማን፡ነው፧
30፤ይህም፡ዝንጉ፡ሰው፡እንዳይነግሥ፥
ሕዝቡም፡የሚያጠምድ፡እንዳይኖር፡ነው።
31፤እግዚአብሔርን፦እኔ፡ሳልበድል፡ቅጣት፡ተቀበልኹ፤
32፤የማላየውን፡ነገር፡አንተ፡አስተምረኝ፤
ኀጢአትንም፡ሠርቼ፡እንደ፡ኾነ፥
ደግሜ፡አልሠራም፡የሚለው፡ማን፡ነው፧
33፤በእውኑ፡አንተ፡ጥለኸዋልና፥
ፍዳው፡አንተ፡እንደምትወደ፟ው፡ይኾናልን፧
አንተ፡ትመርጣለኽ፡እንጂ፡እኔ፡አይደለኹም፤
ስለዚህ፡የምታውቀውን፡ተናገር።
34፤የሚሰሙኝ፡ጥበበኛዎች፡ዅሉ፥
አስተዋዮችም፡እንዲህ፡ይሉኛል።
35፤ኢዮብ፡ያለዕውቀት፡ተናግሯል፥
ቃሉም፡በአእምሮ፡አይደለችም።
36፤ኢዮብ፡እስከ፡ፍጻሜ፡ድረስ፡ምነው፡በተፈተነ፡ኖሮ!
ርሱ፡እንደ፡ክፉዎች፡መልሷልና፤
37፤በኀጢአቱም፡ላይ፡ዐመፅን፡ጨምሯልና፥
በእኛም፡መካከል፡በእጁ፡ያጨበጭባልና፥
ቃልንም፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ያበዛልና።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡35።______________
ምዕራፍ፡35።
1፤ኤሊሁም፡ደግሞ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ይህ፡ጽድቅ፡እንደ፡ኾነ፡ታስባለኽን፧
ወይስ፦በእግዚአብሔር፡ፊት፡እኔ፡ጻድቅ፡ነኝ፡ትላለኽን፧
3፤አንተ፦ምን፡ጥቅም፡አለኽ፧
ኀጢአት፡ሠርቼ፡ከማገኘው፡ይልቅ፡ኀጢአት፡ባልሠራ፡ኖሮ፡ምን፡እጠቀማለኹ፧ብለኽ፡ጠይቀኻልና።
4፤እኔ፡ለአንተና፡ከአንተ፡ጋራ፡ላሉ፡ለባልንጀራዎችኽ፡እመልሳለኹ።
5፤ዐይኖችኽን፡ወደ፡ሰማይ፡አቅንተኽ፡እይ፤
ከአንተም፡ከፍ፡ከፍ፡ያሉትን፡ደመናት፡ተመልከት።
6፤ኀጢአት፡ብትሠራ፡ምን፡ትጐዳዋለኽ፧
መተላለፍኽስ፡ቢበዛ፡ምን፡ታደርገዋለኽ፧
7፤ጻድቅስ፡ብትኾን፡ምን፡ትሰጠዋለኽ፧
ወይስ፡ከእጅኽ፡ምንን፡ይቀበላል፧
8፤እንደ፡አንተ፡ያለውን፡ሰው፡ክፋትኽ፡ይጐዳዋል፤
ለሰውም፡ልጅ፡ጽድቅኽ፡ይጠቅመዋል።
9፤ከግፍ፡ብዛት፡የተነሣ፡ሰዎች፡ይጮኻሉ፤
ከኀያላንም፡ክንድ፡የተነሣ፡ለርዳታ፡ይጠራሉ።
10፤11፤ነገር፡ግን፦በሌሊት፡መዝሙርን፡የሚሰጥ፥
ከምድርም፡እንስሳዎች፡ይልቅ፡የሚያስተምረን፡
ከሰማይም፡ወፎች፡ይልቅ፡ጥበበኛዎች፡የሚያደርገን፤
ፈጣሪዬ፡እግዚአብሔር፡ወዴት፡ነው፧የሚል፡የለም።
12፤በዚያ፡ስለ፡ክፉ፡ሰዎች፡ትዕቢት፡ይጮኻሉ፥
ርሱ፡ግን፡አይመልስላቸውም።
13፤በእውነት፡እግዚአብሔር፡ከንቱ፡ነገርን፡አይሰማም፥
ዅሉን፡የሚችል፡አምላክም፡አይመለከተውም፤
14፤ይልቁንም፦አላየውም፤
ነገሩ፡በርሱ፡ፊት፡ነው፥እኔም፡አጠብቀዋለኹ፡ስትል።
15፤አኹን፡ግን፡በቍጣው፡አልጐበኘምና።
በኀጢአት፡እጅግ፡አያስብም፡ትላለኽ።
16፤ስለዚህ፥ኢዮብ፡አፉን፡በከንቱ፡ይከፍታል፥
ያለዕውቀትም፡ቃሉን፡ያበዛል።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡36።______________
ምዕራፍ፡36።
1፤ኤሊሁም፡ደግሞ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ገና፡ስለ፡እግዚአብሔር፡የሚነገር፡አለኝና፡
ጥቂት፡ቈየኝ፥እኔም፡አስታውቅኻለኹ።
3፤ዕውቀቴን፡ከሩቅ፡አመጣለኹ፥
ፈጣሪዬንም፦ጻድቅ፡ነው፡እላለኹ።
4፤ቃሌ፡በእውነት፡ያለሐሰት፡ነው፤
በዕውቀትም፡ፍጹም፡የኾነ፡ከአንተ፡ጋራ፡አለ።
5፤እንሆ፥እግዚአብሔር፡ኀያል፡ነው፥ማንንም፡አይንቅም፤
ርሱም፡በማስተዋል፡ብርታት፡ኀያል፡ነው።
6፤ርሱ፡የበደለኛዎችን፡ሕይወት፡አያድንም፤
ለችግረኛዎች፡ግን፡ፍርዱን፡ይሰጣል።
7፤ዐይኑን፡ከጻድቃን፡ላይ፡አያርቅም፤
ለዘለዓለምም፡ከነገሥታት፡ጋራ፡በዙፋን፡ላይ፡ያስቀምጣቸዋል፥
እነርሱም፡ከፍ፡ከፍ፡ይላሉ።
8፤በሰንሰለት፡ቢታሰሩ፥
ወይም፡በችግር፡ገመድ፡ቢጠመዱ፥
9፤ሥራቸውንና፡መተላለፋቸውን፡
በትዕቢትም፡እንዳደረጉ፡ይናገራቸዋል።
10፤ዦሯቸውን፡ለተግሣጽ፡ይከፍተዋል፥
ከኀጢአትም፡ይመለሱ፡ዘንድ፡ያዛ፟ቸዋል።
11፤ቢሰሙ፡ቢያገለግሉትም፥
ዕድሜያቸውን፡በልማት፥
ዘመናቸውንም፡በተድላ፡ይፈጽማሉ።
12፤ባይሰሙ፡ግን፡በሰይፍ፡ይጠፋሉ፥
ያለዕውቀትም፡ይሞታሉ።
13፤ዝንጉዎች፡ግን፡ቍጣን፡ያዘጋጃሉ፤
ርሱም፡ባሰራቸው፡ጊዜ፡አይጮኹም።
14፤በሕፃንነታቸው፡ሳሉ፡ይሞታሉ፥
ሕይወታቸውም፡በሰዶማውያን፡መካከል፡ይጠፋል።
15፤የተቸገረውን፡በችግሩ፡ያድነዋል፤
በመከራም፡ዦሯቸውን፡ይገልጣል።
16፤እንዲሁም፡አንተን፡ከመከራ፡
ችግር፡ወደሌለበት፡ወደ፡ሰፊ፡ስፍራ፡በወሰደኽ፡ነበር፥
በማእዱኽ፡ላይ፡የተዘጋጀውም፡ስብ፡በሞላበት፡ነበር።
17፤አንተ፡ግን፡በበደለኛዎች፡ፍርድ፡የተሞላኽ፡ነኽ፤
ስለዚህ፡ፍርድና፡ብይን፡ይይዝኻል።
18፤ቍጣ፡ለስድብ፡አያታል፟ኽ፤
የማማለጃም፡ብዛት፡ፈቀቅ፡አያድርግኽ።
19፤ባለጠግነትኽ፡የኀይልኽም፡ብርታት፡ዅሉ፡
ያለችግር፡እንድትኾን፡ሊረዳኽ፡ይችላልን፧
20፤ወገኖች፡ከስፍራቸው፡የሚወጡበትን፡ሌሊት፡አትመኝ።
21፤ከመከራ፡ይልቅ፡ይህን፡መርጠኻልና፥
ኀጢአትን፡እንዳትመለከት፡ተጠንቀቅ።
22፤እንሆ፥እግዚአብሔር፡በኀይሉ፡ከፍ፡ያለውን፡ነገር፡ያደርጋል፤
እንደ፡ርሱስ፡ያለ፡አስተማሪ፡ማን፡ነው፧
23፤መንገዱን፡ማን፡አዘዘለት፧
ወይስ፦ኀጢአትን፡ሠርተኻል፡የሚለው፡ማን፡ነው፧
24፤ሰዎች፡የዘመሩትን፡ሥራውን፡ታከብር፡ዘንድ፡ዐስብ።
25፤ሰዎች፡ዅሉ፡ተመልክተውታል፤
ሰውም፡ከሩቅ፡ያየዋል።
26፤እንሆ፥እግዚአብሔር፡ታላቅ፡ነው፥እኛም፡አናውቀውም።
የዘመኑም፡ቍጥር፡አይመረመርም።
27፤የውሃውን፡ነጠብጣብ፡ወደ፡ላይ፡ይስባል፥
ዝናብም፡ከጉም፡ይንጠባጠባል፤
28፤ደመናት፡ያዘንባሉ፥
በሰዎችም፡ላይ፡በብዙ፡ያንጠባጥባሉ።
29፤የደመናውንም፡መዘርጋት፥
የማደሪያውንም፡ነጐድጓድ፡የሚያስተውል፡ማን፡ነው፧
30፤እንሆ፥በዙሪያው፡ብርሃኑን፡ይዘረጋል፤
የባሕሩንም፡ጥልቀት፡ይከድናል።
31፤በእነዚህ፡በአሕዛብ፡ላይ፡ይፈርዳል፤
ብዙም፡ምግብ፡ይሰጣል።
32፤እጆቹን፡በብርሃን፡ይሰውራል፥
በጠላቱም፡ላይ፡ይወጣ፡ዘንድ፡ያዘ፟ዋል፤
33፤የነጐድጓድ፡ድምፅ፡ስለ፡ርሱ፡ይናገራል፤
እንስሳዎችም፡ደግሞ፡ስለሚመጣው፡ውሽንፍር፡ይጮኻሉ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡37።______________
ምዕራፍ፡37።
1፤ስለዚህም፡ልቤ፡ተንቀጠቀጠ፥
ከስፍራውም፡ተንቀሳቀሰ።
2፤የድምፁን፡መትመም፡ስሙ፥
ከአፉም፡የሚወጣውን፡ጕርምርምታ፡አድምጡ።
3፤ርሱን፡ወደ፡ሰማያት፡ዅሉ፡ታች፥
ብርሃኑንም፡ወደ፡ምድር፡ዳርቻ፡ይሰዳ፟ል።
4፤በስተዃላው፡ድምፅ፡ይጮኻል፤
በግርማውም፡ድምፅ፡ያንጐደጕዳል፤
ድምፁም፡በተሰማ፡ጊዜ፡
መብረቁን፡አይከለክልም።
5፤እግዚአብሔር፡በድምፁ፡ድንቅኛ፡ያንጐደጕዳል፤
እኛም፡የማናስተውለውን፡ታላቅ፡ነገር፡ያደርጋል።
6፤በረዶውንና፡ውሽንፍሩን፡ብርቱንም፡ዝናብ፦
በምድር፡ላይ፡ውደቁ፡ይላል።
7፤ሰው፡ዅሉ፡ሥራውን፡ያውቅ፡ዘንድ፡
የሰውን፡ዅሉ፡እጅ፡ያትማል።
8፤አውሬዎቹም፡ወደ፡ጫካው፡ይገባሉ፥
በዋሾቻቸውም፡ይቀመጣሉ።
9፤ከተሰወረ፡ማደሪያውም፡ዐውሎ፡ነፋስ፥
ከሰሜንም፡ብርድ፡ይወጣል።
10፤ከእግዚአብሔር፡እስትንፋስ፡ውርጭ፡ተሰጥቷል፤
የውሃዎችም፡ስፋት፡ይጠባ፟ል።
11፤የውሃውንም፡ሙላት፡በደመና፡ላይ፡ይጭናል፤
የብርሃኑንም፡ደመና፡ይበታትናል፤
12፤13፤ለተግሣጽ፡ወይም፡ለምድሩ፡ወይም፡ለምሕረት፡ቢኾን፥
ሰው፡በሚኖርበት፡ዓለም፡ላይ፡
ያዘዘውን፡ዅሉ፡ያደርግ፡ዘንድ፡
ፈቃዱ፡ወደ፡መራችው፡ይዞራል።
14፤ኢዮብ፡ሆይ፥ይህን፡ስማ፤
ቁም፥የእግዚአብሔርንም፡ተኣምራት፡ዐስብ።
15፤በእውኑ፡እግዚአብሔር፡እንዴት፡እንደሚያዛ፟ቸው፥
የደመናውንም፡ብርሃን፡እንዴት፡እንደሚያበራ፡ዐውቀኻልን፧
16፤ወይስ፡የደመናውን፡ሚዛን፥
ወይስ፡በዕውቀት፡ፍጹም፡የኾነውን፡ተኣምራት፡ዐውቀኻልን፧
17፤በደቡብ፡ነፋስ፡ምድር፡ጸጥ፡ባለች፡ጊዜ፥
ልብስኽ፡የሞቀች፡አንተ፡ሆይ፥
18፤እንደ፡ቀለጠ፡መስተዋት፡
ብርቱ፡የኾኑትን፡ሰማያት፡ከርሱ፡ጋራ፡ልትዘረጋ፡ትችላለኽን፧
19፤እኛ፡ከጨለማ፡የተነሣ፡በሥርዐት፡መናገር፡አንችልምና፥
የምንለውን፡አስታውቀን።
20፤ማንም፡በርሱ፡ላይ፡ቢናገር፡ፈጽሞ፡ይዋጣልና፥
እኔ፡እናገር፡ዘንድ፡ብወድ፟፡ሰው፡ይነግረዋልን፧
21፤አኹንም፡ነፋስ፡ዐልፎ፡ካጠራ፟ቸው፡በዃላ፥
ሰው፡በሰማያት፡የሚበራውን፡ብርሃን፡ሊመለከት፡አይችልም።
22፤ከሰሜን፡ወርቅ፡የሚመስል፡ጌጠኛ፡ብርሃን፡ይወጣል፤
በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡የሚያስፈራ፡ግርማ፡አለ።
23፤ዅሉን፡የሚችል፡አምላክን፡እናገኝ፡ዘንድ፡አንችልም፤
በኀይል፡ታላቅ፡ነው፤
በፍርድና፡በጽድቅም፡አያስጨንቅም።
24፤ስለዚህ፥ሰዎች፡ይፈሩታል፤
በልባቸውም፡ጠቢባን፡የኾኑትን፡ዅሉ፡አይመለከትም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡38።______________
ምዕራፍ፡38።
1፤እግዚአብሔርም፡በዐውሎ፡ነፋስ፡ውስጥ፡ኾኖ፡ለኢዮብ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
2፤ያለዕውቀት፡በሚነገር፡ቃል፡
ምክርን፡የሚያጨልም፡ይህ፡ማነው፧
3፤እንግዲህ፡እንደ፡ሰው፡ወገብኽን፡ታጠቅ፤
እጠይቅኻለኹ፥አንተም፡ተናገረኝ።
4፤ምድርን፡በመሠረትኹ፡ጊዜ፡አንተ፡ወዴት፡ነበርኽ፧
ታስተውል፡እንደ፡ኾንኽ፡ተናገር።
5፤ብታውቅስ፡መሠፈሪያዋን፡የወሰነ፥
በላይዋስ፡የመለኪያ፡ገመድ፡የዘረጋ፡ማን፡ነው፧
6፤7፤አጥቢያ፡ኮከቦች፡በአንድነት፡ሲዘምሩ፥
የእግዚአብሔርም፡ልጆች፡ዅሉ፡እልል፡ሲሉ፥
መሠረቶቿ፡በምን፡ላይ፡ተተክለው፡ነበር፧
የማእዘኗንስ፡ድንጋይ፡ያቆመ፡ማን፡ነው፧
8፤ከማሕፀን፡እንደሚወጣ፡በወጣ፡ጊዜ፡
ባሕርን፡በመዝጊያዎች፡የዘጋ፡ማን፡ነው፧
9፤ደመናውን፡ለልብሱ፥
ጨለማንም፡ለመጠቅለያው፡አደረግኹ፤
10፤ድንበሩን፡በዙሪያው፡አድርጌ፥
መወርወሪያዎቹንና፡መዝጊያዎቹን፡አኑሬ።
11፤እስከዚህ፡ድረስ፡ድረሺ፥አትለፊ፤
በዚህም፡ለትዕቢተኛው፡ማዕበልሽ፡ገደብ፡ይኹን፡አልኹ።
12፤13፤የምድርን፡ዳርቻ፡ይይዝ፡ዘንድ፥
ከርሷም፡በደለኛዎች፡ይናወጡ፡ዘንድ፥
በእውኑ፡ከተወለድኽ፡ዠምሮ፡ማለዳን፡አዘ፟ኻልን፧
ለወገግታም፡ስፍራውን፡አስታወቀኸዋልን፧
14፤ጭቃ፡ከማኅተም፡በታች፡እንደሚለወጥ፡እንዲሁ፡ርሷ፡ትለወጣለች፤
ነገርም፡ዅሉ፡እንደ፡ልብስ፡ተቀልሟል።
15፤ከበደለኛዎች፡ብርሃናቸው፡ተከልክሏል፥
ከፍ፡ያለውም፡ክንድ፡ተሰብሯል።
16፤ወደባሕር፡ምንጭስ፡ውስጥ፡ገብተኻልን፧
በቀላዩስ፡መሠረት፡ውስጥ፡ተመላልሰኻልን፧
17፤የሞት፡በሮች፡ተገልጠውልኻልን፧
የሞትንስ፡ጥላ፡ደጆች፡አይተኻልን፧
18፤ምድርንስ፡በስፋቷ፡አስተውለኻታልን፧
ዅሉን፡ዐውቀኽ፡እንደ፡ኾነ፡ተናገር።
19፤20፤ወደ፡ዳርቻው፡ትነዳው፡ዘንድ፥
ወደ፡ቤቱም፡የሚያደርሰውን፡ጐዳና፡ታውቅ፡ዘንድ፥
የብርሃን፡መኖሪያ፡መንገድ፡የት፡ነው፧
የጨለማውስ፡ቦታ፡ወዴት፡አለ፧
21፤በዚያን፡ጊዜ፡ተወልደኽ፡ነበርና፥
የዕድሜኽም፡ቍጥር፡ብዙ፡ነውና፤
በእውነት፡አንተ፡ሳታውቅ፡አትቀርም።
22፤በእውኑ፡ወደበረዶው፡ቤተ፡መዛግብት፡ገብተኻልን፧
የበረዶውንስ፡ቅንጣት፡ቤተ፡መዛግብት፡አይተኻልን፧
23፤ይኸውም፡ለመከራ፡ጊዜ፡ለሰልፍና፡ለጦርነት፡ቀን፡የጠበቅኹት፡ነው።
24፤ብርሃንስ፡በምን፡መንገድ፡ይከፈላል፧
የምሥራቅስ፡ነፋስ፡በምድር፡ላይ፡እንዴት፡ይበተናል፧
25፤26፤ባድማውንና፡ውድማውን፡እንዲያጠግብ፥
27፤ሣሩንም፡እንዲያበቅል፥
ማንም፡በሌለባት፡ምድር፡ላይ፥
ሰውም፡በሌለባት፡ምድረ፡በዳ፡ላይ፡ዝናብን፡ያዘንብ፡ዘንድ፥
ለፈሳሹ፡ውሃ፡መንዶልዶያውን፥
ወይስ፡ለሚያንጐደጕድ፡መብረቅ፡መንገድን፡ያበጀ፡ማን፡ነው፧
28፤በእውኑ፡ለዝናብ፡አባት፡አለውን፧
ወይስ፡የጠልን፡ነጠብጣብ፡የወለደ፡ማን፡ነው፧
29፤በረዶስ፡ከማን፡ማሕፀን፡ወጣ፧
የሰማዩንስ፡ዐመዳይ፡ማን፡ወለደው፧
30፤ውሃዎች፡እንደ፡ድንጋይ፡ጠነከሩ፥
የቀላዩም፡ፊት፡ረግቷል።
31፤በእውኑ፡የሰባቱን፡ከዋክብት፡ዘለላ፡ታስር፡ዘንድ፥
ወይስ፡ኦሪዮን፡የሚባለውን፡ኮከብ፡ትፈታ፡ዘንድ፡ትችላለኽን፧
32፤ወይስ፡ማዛሮት፡የሚባሉትን፡ከዋክብት፡በጊዜያቸው፡ታወጣ፡ዘንድ፥
ወይስ፡ድብ፡የሚባለውን፡ኮከብ፡ከልጆቹ፡ጋራ፡ትመራ፡ዘንድ፡ትችላለኽን፧
33፤የሰማይን፡ሥርዐት፡ታውቃለኽን፧
በምድርስ፡ለይ፡እንዲሠለጥን፡ልታደርግ፡ትችላለኽን፧
34፤የውሃዎች፡ብዛት፡ይሸፍንኽ፡ዘንድ፡
ቃልኽን፡ወደ፡ደመናት፡ታነሣ፡ዘንድ፡ትችላለኽን፧
35፤መብረቆች፡ኼደው፦እንሆ፥እዚህ፡አለን፡ይሉኽ፡ዘንድ፡
ልትልካቸው፡ትችላለኽን፧
36፤በውስጡስ፡ጥበብን፡ያኖረ፥
ለሰውስ፡ልብ፡ማስተዋልን፡የሰጠ፡ማን፡ነው፧
37፤38፤የሰማይን፡ደመና፡በጥበቡ፡ሊቈጥር፡የሚችል፡ማን፡ነው፧
ትቢያ፡በተበጠበጠ፡ጊዜ፥
ጓሎቹም፡በተጣበቁ፡ጊዜ፥
የሰማይን፡ረዋት፡ሊያዘነብል፡የሚችል፡ማን፡ነው፧
39፤40፤በዋሾቻቸው፡ውስጥ፡ተጋድመው፥
በጫካም፡ውስጥ፡አድብተው፡ሳሉ፥
ለአንበሳዪቱ፡አደን፡ታድናለኽን፧
የልጆቿንስ፡ነፍስ፡ታጠግብ፡ዘንድ፡ትችላለኽን፧
41፤ልጆቹ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ሲጮኹ፥
የሚበሉትም፡ዐጥተው፡ሲቅበዘበዙ፥
ለቍራ፡መብልን፡የሚሰጠው፡ማን፡ነው፧
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡39።______________
ምዕራፍ፡39።
1፤የበረሓ፡ፍየል፡የምትወልድበትን፡ጊዜ፡ታውቃለኽን፧
ዋላዪቱስ፡የምታምጥበትን፡ጊዜ፡ትመለከታለኽን፧
2፤ርሷ፡የምትፈጽመውንስ፡ወራት፡ትቈጥራለኽን፧
የምትወልድበትንስ፡ጊዜ፡ታውቃለኽን፧
3፤ይንበረከካሉ፥ልጆቻቸውንም፡ይወልዳሉ፥
ከምጣቸውም፡ያርፋሉ።
4፤ልጆቻቸው፡ይጠነክራሉ፥
በሜዳም፡ያድጋሉ፤
ይወጣሉ፥ወደ፡እነርሱም፡አይመለሱም።
5፤የሜዳውስ፡አህያ፡ሐራነት፡ማን፡አወጣው፧
የበረሓውንስ፡አህያ፡ከእስራቱ፡ማን፡ፈታው፧
6፤በረሓውን፡ለርሱ፡ቤት፡አድርጌ፡ሰጠኹት፤
መኖሪያውም፡በጨው፡ምድር፡ነው።
7፤በከተማ፡ውካታ፡ይዘብታል፤
የነጂውን፡ጩኸት፡አይሰማም።
8፤ተራራውን፡እንደ፡መሰምሪያው፡ይመለከተዋል፥
ለምለሙንም፡ዅሉ፡ይፈልጋል።
9፤ጐሽ፡ያገለግልኽ፡ዘንድ፡ይታዘዛልን፧
ወይስ፡በግርግምኽ፡አጠገብ፡ያድራልን፧
10፤ጐሽ፡ይተልምልኽ፡ዘንድ፡ትጠምደዋለኽን፧
ወይስ፡ከአንተ፡በዃላ፡በዕርሻ፡ላይ፡ይጐለጕላልን፧
11፤ጕልበቱስ፡ብርቱ፡ስለ፡ኾነ፡ትታመነዋለኽን፧
ተግባርኽንስ፡ለርሱ፡ትተዋለኽን፧
12፤ዘርኽንስ፡ይመልስልኽ፡ዘንድ፥
በዐውድማኽስ፡ያከማችልኽ፡ዘንድ፡ትታመነዋለኽን፧
13፤የሰጐን፡ክንፍ፡በደስታ፡ይንቀሳቀሳል፤
ነገር፡ግን፡ክንፉና፡ላባው፡ጭምተኛ፡ነውን፧
14፤ዕንቍላሏን፡በመሬት፡ላይ፡ትተዋለች፥
በዐፈርም፡ውስጥ፡ታሞቀዋለች፤
15፤እግር፡ይሰብረው፡ዘንድ፥
የምድረ፡በዳም፡አውሬ፡ይረግጠው፡ዘንድ፡ትረሳለች።
16፤የርሷ፡እንዳልኾኑ፡በልጆቿ፡ትጨክናለች።
በከንቱም፡ብትሠራ፡አትፈራም፤
17፤እግዚአብሔር፡ጥበብን፡ከርሷ፡ከልክሏልና፥
ማስተዋልንም፡አልሰጣትምና።
18፤ወደ፡ላይ፡ከፍ፡ከፍ፡ስትል፡
በፈረስና፡በፈረሰኛው፡ትሳለቃለች።
19፤ለፈረስ፡ጕልበቱን፡ሰጥተኸዋልን፧
ዐንገቱንስ፡ጋማ፡አልብሰኸዋልን፧
20፤እንደ፡አንበጣስ፡አፈናጠርኸውን፧
የማንኰራፋቱ፡ክብር፡የሚያስፈራ፡ነው።
21፤በኰቴው፡በሸለቆው፡ውስጥ፡ይጐደፍራል፥
በጕልበቱም፡ደስ፡ይለዋል፤
ሰይፍም፡የታጠቁትን፡ለመገናኘት፡ይወጣል።
22፤በፍርሀት፡ላይ፡ይሥቃል፥
ርሱም፡አይደነግጥም፤
ከሰይፍም፡ፊት፡አይመለስም።
23፤በርሱ፡ላይ፡የፍላጻ፡ኰረጆና፡ብልጭልጭ፡የሚል፡ጦር፡
ሠላጢንም፡ያንኳኳሉ።
24፤በጭካኔና፡በቍጣ፡መሬትን፡ይውጣል፤
የመለከትም፡ድምፅ፡ቢሰማ፡አይቆምም።
25፤የመለከትም፡ድምፅ፡ሲሰማ፦ዕሠይ! ይላል፤
ከሩቅ፡ኾኖ፡ሰልፍንና፡የአለቃዎቹን፡ጩኸት፥
የሰራዊቱንም፡ውካታ፡ያሸታል።
26፤በእውኑ፡ከጥበብኽ፡የተነሣ፡ጭልፊት፡ያንዣብባልን፧
ወይስ፡ክንፎቹን፡ወደ፡ደቡብ፡ይዘረጋልን፧
27፤በአፍኽ፡ትእዛዝ፡ንስር፡ከፍ፡ከፍ፡ይላልን፧
ቤቱንስ፡በአርያም፡ላይ፡ያደርጋልን፧
28፤በገደል፡ላይ፡ይኖራል፤
በገደሉ፡ገመገምና፡በጥጉ፡ያድራል።
29፤በዚያም፡ኾኖ፡የሚነጥቀውን፡ይጐበኛል፤
ዐይኑም፡በሩቅ፡ትመለከታለች።
30፤ጫጩቶቹም፡ደም፡ይጠጣሉ፤
በድን፡ባለባትም፡ስፍራ፡ርሱ፡በዚያ፡አለ።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡40።______________
ምዕራፍ፡40።
1፤እግዚአብሔርም፡መለሰ፡ኢዮብንም፡እንዲህ፡አለው፦
2፤በእውኑ፡የሚከራከር፡ሰው፡ዅሉን፡ከሚችል፡አምላክ፡ጋራ፡ይከራከራልን፧
ከእግዚአብሔር፡ጋራ፡የሚዋቀስ፡ርሱ፡ይመልስለት።
3፤ኢዮብም፡መለሰ፡እግዚአብሔርንም፡እንዲህ፡አለው፦
4፤እንሆ፥እኔ፡ወራዳ፡ሰው፡ነኝ፤የምመልስልኽ፡ምንድር፡ነው፧
እጄን፡በአፌ፡ላይ፡እጭናለኹ።
5፤አንድ፡ጊዜ፡ተናገርኹ፥አልመልስምም፤
ኹለተኛ፡ጊዜም፥ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አልናገርም።
6፤እግዚአብሔርም፡በዐውሎ፡ነፋስ፡ውስጥ፡ኾኖ፡ለኢዮብ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦
7፤እንግዲህ፡እንደ፡ወንድ፡ወገብኽን፡ታጠቅ፤
እጠይቅኻለኹ፥አንተም፡ተናገረኝ።
8፤በእውኑ፡ፍርዴን፡ታፈርሳለኽን፧
አንተስ፡ጻድቅ፡ትኾን፡ዘንድ፡በእኔ፡ትፈርዳለኽን፧
9፤እንደእግዚአብሔር፡ክንድ፡ያለ፡ክንድ፡አለኽን፧
ወይስ፡እንደ፡ርሱ፡ባለ፡ድምፅ፡ታንጐደጕዳለኽን፧
10፤በታላቅነትና፡በልዕልና፡ተላበስ፤
በክብርና፡በግርማም፡ተጐናጸፍ።
11፤የቍጣኽን፡ፈሳሽ፡አፍስ፟፤
ትዕቢተኛውንም፡ዅሉ፡ተመልክተኽ፡አዋርደው።
12፤ትዕቢተኛውንም፡ዅሉ፡ተመልከት፥ዝቅ፡ዝቅም፡አድርገው፤
በደለኛዎችንም፡ወዲያውኑ፡ርገጣቸው።
13፤በዐፈር፡ውስጥ፡በአንድነት፡ሰውራቸው፤
በተሸሸገም፡ስፍራ፡ፊታቸውን፡ሸፍን።
14፤በዚያን፡ጊዜም፡ቀኝ፡እጅኽ፡ታድንኽ፡ዘንድ፡እንድትችል፡
እኔ፡ደግሞ፡እመሰክርልኻለኹ።
15፤ከአንተ፡ጋራ፡የሠራኹትን፡ጕማሬ፥እስኪ፥ተመልከት፤
እንደ፡በሬ፡ሣር፡ይበላል።
16፤እንሆ፥ብርታቱ፡በወገቡ፡ውስጥ፡ነው፤
ኀይሉም፡በሆዱ፡ዥማት፡ውስጥ፡ነው።
17፤ዥራቱን፡እንደ፡ጥድ፡ዛፍ፡ያወዛውዛል፤
የወርቹ፡ዥማት፡የተጐነጐነ፡ነው።
18፤ዐጥንቱ፡እንደ፡ናስ፡አገዳ፡ነው፤
አካላቱ፡እንደ፡ብረት፡ዘንጎች፡ናቸው።
19፤ርሱ፡የእግዚአብሔር፡ፍጥረት፡አውራ፡ነው፤
ሠሪውም፡ሰይፉን፡ሰጠው።
20፤የሜዳ፡እንስሳዎች፡ዅሉ፡የሚጫወቱበት፡ተራራ፡
ምግብን፡ያበቅልለታል።
21፤ጥላ፡ካለው፡ዛፍ፡በታች፥
በደንገልና፡በረግረግ፡ውስጥ፡ይተኛል።
22፤ጥላ፡ያለው፡ዛፍ፡በጥላው፡ይሰውረዋል፤
የወንዝ፡አሓያ፡ዛፎች፡ይከቡ፟ታል።
23፤እንሆ፥ወንዙ፡ቢጐርፍ፡አይደነግጥም፤
ዮርዳኖስም፡እስከ፡አፉ፡ድረስ፡ቢፈስ፟፡ርሱ፡ይተማመናል።
24፤ዐይኖቹ፡እያዩ፡ይያዛልን፧
አፍንጫውስ፡በወጥመድ፡ይበሳልን፧
25፤በእውኑ፡አዞውን፡በመቃጥን፡ታወጣለኽን፧
ምላሱንስ፡በገመድ፡ታስረዋለኽን፧
26፤ወይስ፡ስናጋ፡በአፍንጫው፡ታደርጋለኽን፧
ወይስ፡በችንካር፡ጕንጩን፡ትበሳለኽን፧
27፤በእውኑ፡ወዳንተ፡እጅግ፡ይለምናልን፧
በጣፈጠስ፡ቃል፡ይናገርኻልን፧
28፤በእውኑ፡ከአንተ፡ጋራ፡ቃል፡ኪዳን፡ይገባልን፧
ወይስ፡ለዘለዓለም፡ባሪያ፡ታደርገዋለኽን፧
29፤ከወፍ፡ጋራ፡እንደምትጫወት፡ከርሱ፡ጋራ፡ትጫወታለኽን፧
ወይስ፡ለሴት፡ባሪያዎችኽ፡ታስረዋለኽን፧
30፤አጥማጆች፡በርሱ፡ይከራከራሉን፧
ወይስ፡ነጋዴዎች፡ያካፍሉታልን፧
31፤በእውኑ፡ቍርበቱን፡በጭሬ፥
ራሱንስ፡በዓሣ፡ጦር፡ትሞላዋለኽን፧
32፤እጅኽን፡በላዩ፡ጫን፤
ሰልፉን፡ዐስብ፥እንግዲህም፡አትድገም።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡41።______________
ምዕራፍ፡41።
1፤እንሆ፥ተስፋው፡ከንቱ፡ነው፤
ያየው፡ዅሉ፡ስንኳ፡በፊቱ፡ይዋረዳል።
2፤ያንቀሳቅሰውም፡ዘንድ፡የሚደፍር፡የለም፤
እንግዲህ፡በፊቴ፡መቆም፡የሚችል፡ማን፡ነው፧
3፤እመልስለትስ፡ዘንድ፡መዠመሪያ፡የሰጠኝ፡ማን፡ነው፧
ከሰማይ፡ዅሉ፡በታች፡ያለው፡ገንዘቤ፡ነው።
4፤ስለ፡አካላቱና፡ስለ፡ብርቱ፡ኀይሉ፥
ስለ፡መልካም፡ሰውነቱ፡ዝም፡አልልም።
5፤የውጪ፡ልብሱን፡ማን፡ይገፋል፧
በጥንድ፡መንጋጋውስ፡ውስጥ፡ማን፡ይገባል፧
6፤የፊቱንስ፡ደጆች፡የሚከፍት፡ማን፡ነው፧
በጥርሶቹ፡ዙሪያ፡ግርማ፡አለ።
7፤ቅርፊቶቹ፡ጠንካራ፡ስለ፡ኾኑ፡ርሱ፡ትዕቢተኛ፡ነው፤
በጠባብ፡ማተሚያ፡እንደ፡ታተሙ፡ናቸው።
8፤ርስ፡በርሳቸው፡የተቀራረቡ፡ናቸውና፥
ነፋስ፡በመካከላቸው፡መግባት፡አይችልም።
9፤ርስ፡በርሳቸው፡የተገጣጠሙ፡ናቸው፤
እስከማይለያዩም፡ድረስ፡ተያይዘዋል።
10፤እንጥሽታው፡ብልጭታ፡ያወጣል፥
ዐይኖቹም፡እንደ፡ወገግታ፡ናቸው።
11፤ከአፉ፡ፋናዎች፡ይወጣሉ፥
የእሳትም፡ፍንጣሪ፡ይረጫል።
12፤እንደ፡ፈላ፡ድስትና፡እንደሚቃጠል፡ሸምበቆ፡
ከአንፍንጫው፡ጢስ፡ይወጣል።
13፤እስትንፋሱ፡ከሰልን፡ታቃጥላለች፥
ነበልባልም፡ከአፉ፡ይወጣል።
14፤በዐንገቱ፡ኀይል፡ታድራለች፤
ግርማ፡በፊቱ፡ይዘፍናል።
15፤የሥጋውም፡ቅርፊት፡የተጣበቀ፡ነው፤
እስከማይንቀሳቀሱም፡ድረስ፡በርሱ፡ላይ፡ጸንተዋል።
16፤ልቡ፡እንደ፡ድንጋይ፡የደነደነ፡ነው፤
እንደ፡ወፍጮ፡ድንጋይ፡የጸና፡ነው።
17፤በተነሣ፡ጊዜ፡ኀያላን፡ይፈራሉ፤
ከድንጋጤም፡የተነሣ፡ያብዳሉ።
18፤ሰይፍና፡ጦር፥ፍላጻና፡መውጊያም፡ቢያገኙት፡አያሸንፉትም።
19፤ብረትን፡እንደ፡ገለባ፥
ናስንም፡እንደ፡ነቀዘ፡ዕንጨት፡ይቈጥራቸዋል።
20፤ፍላጻ፡ሊያባርረው፡አይችልም፤
የወንጭፍም፡ድንጋዮች፡እንደ፡ገለባ፡ይኾኑለታል።
21፤በሎታውን፡እንደ፡ገለባ፡ይቈጥረዋል፤
ሠላጢኑም፡ሲሰበቅ፡ይሥቃል።
22፤ታቹ፡እንደ፡ስለታም፡ገል፡ነው፤
እንደ፡መዳመጫም፡በጭቃ፡ላይ፡ያልፋል።
23፤ቀላዩን፡እንደ፡ድስት፡ያፈላዋል፤
ባሕሩንም፡እንደ፡ሽቱ፡ምንቸት፡ያደርገዋል።
24፤በስተዃላው፡ብሩህ፡መንገድን፡ያበራል፤
ቀላዩም፡ሽበት፡ይመስላል።
25፤ያለፍርሀት፡የተፈጠረ፥
እንደ፡ርሱ፡ያለ፡በምድር፡ላይ፡የለም።
26፤ከፍ፡ያለውን፡ዅሉ፡ይመለከታል፤
በትዕቢተኛዎችም፡ዅሉ፡ላይ፡ንጉሥ፡ነው።
_______________መጽሐፈ፡ኢዮብ፥ምዕራፍ፡42።______________
ምዕራፍ፡42።
1፤ኢዮብም፡መለሰ፡እግዚአብሔርንም፡እንዲህ፡አለው፦
2፤ዅሉን፡ታደርግ፡ዘንድ፡ቻይ፡እንደ፡ኾንኽ፥
ዐሳብኽም፡ይከለከል፡ዘንድ፡ከቶ፡እንደማይቻል፡ዐወቅኹ።
3፤ያለዕውቀት፡ምክርን፡የሚሰውር፡ማን፡ነው፧
ስለዚህ፡እኔ፡የማላስተውለውን፥
የማላውቀውንም፡ድንቅ፡ነገር፡ተናግሬያለኹ።
4፤እባክኽ፥ስማኝ፡እኔም፡ልናገር፤
እጠይቅኽማለኹ፥አንተም፡ተናገረኝ።
5፤መስማትንስ፡በዦሮ፡በመስማት፡ሰምቼ፡ነበር፤
አኹን፡ግን፡ዐይኔ፡አየችኽ፤
6፤ስለዚህ፥ራሴን፡እንቃለኹ፤
በዐፈርና፡በዐመድ፡ላይ፡ተቀምጬ፡እጸጸታለኹ።
7፤እግዚአብሔርም፡ይህን፡ቃል፡ለኢዮብ፡ከተናገረ፡በዃላ፡እግዚአብሔር፡ቴማናዊውን፡ኤልፋዝን፦እንደ፡ባሪያዬ ፡እንደ፡ኢዮብ፡ቅንን፡ነገር፡ስለ፡እኔ፡አልተናገራችኹምና፡ቍጣዬ፡በአንተና፡በኹለቱ፡ባልንጀራዎችኽ፡ላይ፡ ነዷ፟ል።
8፤አኹን፡እንግዲህ፡ሰባት፡ወይፈኖችና፡ሰባት፡አውራ፡በጎች፡ይዛችኹ፡ወደ፡ባሪያዬ፡ወደ፡ኢዮብ፡ዘንድ፡ኺዱ፥ የሚቃጠልንም፡መሥዋዕት፡ስለ፡ራሳችኹ፡አሳርጉ፤ባሪያዬም፡ኢዮብ፡ስለ፡እናንተ፡ይጸልያል፥እኔም፡እንደ፡ስን ፍናችኹ፡እንዳላደርግባችኹ፡ፊቱን፡እቀበላለኹ፤እንደ፡ባሪያዬ፡እንደ፡ኢዮብ፡ቅን፡ነገር፡ስለ፡እኔ፡አልተና ገራችኹምና።
9፤ቴማናዊውም፡ኤልፋዝ፡ሹሐዊውም፡በልዳዶስ፡ናዕማታዊውም፡ሶፋር፡ኼደው፡እግዚአብሔር፡እንዳዘዛቸው፡አደረጉ ፡እግዚአብሔርም፡የኢዮብን፡ፊት፡ተቀበለ።
10፤ኢዮብም፡ስለ፡ወዳጆቹ፡በጸለየ፡ጊዜ፡እግዚአብሔርም፡ምርኮውን፡መለሰለት፤እግዚአብሔርም፡ቀድሞ፡በነበረ ው፡ፋንታ፡ኹለት፡ዕጥፍ፡አድርጎ፡ለኢዮብ፡ሰጠው።
11፤ወንድሞቹና፡እኅቶቹ፡ቀድሞም፡ያውቁት፡የነበሩት፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡መጡ፥በቤቱም፡ከርሱ፡ጋራ፡እንጀራ፡በሉ ፤ስለ፡ርሱም፡ዐዘኑለት፥እግዚአብሔርም፡ካመጣበት፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡አጽናኑት፤እያንዳንዳቸውም፡ብርና፡የወ ርቅ፡ቀለበት፡ሰጡት።
12፤እግዚአብሔርም፡ከፊተኛው፡ይልቅ፡የዃለኛውን፡ለኢዮብ፡ባረከ፤ዐሥራ፡አራት፡ሺሕም፡በጎች፥ስድስት፡ሺሕም ፡ግመሎች፥አንድ፡ሺሕም፡ጥማድ፡በሬዎች፥አንድ፡ሺሕም፡እንስት፡አህያዎች፡ነበሩት።
13፤ደግሞም፡ሰባት፡ወንዶችና፡ሦስት፡ሴቶች፡ልጆች፡ኾኑለት።
14፤የመዠመሪያዪቱንም፡ስም፡ይሚማ፥የኹለተኛዪቱንም፡ስም፡ቃስያ፥የሦስተኛዪቱንም፡ስም፡አማልቶያስ፡ቂራስ፡ ብሎ፡ሰየማቸው።
15፤እንደ፡ኢዮብ፡ሴቶች፡ልጆችም፡ያሉ፡የተዋቡ፡ሴቶች፡በአገሩ፡ዅሉ፡አልተገኙም፤አባታቸውም፡ከወንድሞቻቸው ፡ጋራ፡ርስት፡ሰጣቸው።
16፤ከዚህም፡በዃላ፡ኢዮብ፡መቶ፡አርባ፡ዓመት፡ኖረ፥ልጆቹንና፡የልጅ፡ልጆቹንም፡እስከ፡አራት፡ትውልድ፡ድረስ ፡አየ።
17፤ኢዮብም፡ሸምግሎ፥ዕድሜም፡ጠግቦ፡ሞተ፨

http://www.gzamargna.net